የሕግ አካላትን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ያካተተ የሴቶችን ጾታዊ ጥቃት የመከላከል ዓላማ ያለው ግብረ-ኃይል መቋቋሙን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ ግብረ-ኃይሉ ከቀበሌ ደረጃ ጀምሮ ማኅበረሰቡን የማንቃትና ጥቃት ሲደርስም ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበትን ሥርዓት ከሕግና ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ይዘረጋል።
ይህ የግንኙነት መረብ ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
በዓለም ለ115ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሴቶች ቀን (ማርች 8) አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ የድርጊት መርሐግብር መዘጋጀቱንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የዚህ ዓመቱ የሴቶች ቀን “የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ታስቦ የሚውል ሲሆን፤ ሴቶች በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ለመዘከርና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዱ ፕሮግራሞች ይፋ ይደረጉበታል ተብሏል።
ባለድርሻ አካላት ያስመዘገቡት ውጤት የሚገመገምበትና ተግዳሮቶች ተለይተው መፍትሔ የሚቀመጥበት መድረክ እንደሚሆንም ዶ/ር ኤርጎጌ ገልጸዋል።
በሴቶች ላይ የሚሰሩ ስራዎች የአንድ ቀን ሥራ ብቻ እንዳይሆኑ፣ ወሩን ሙሉ የሚቆዩ ሰፊ ንቅናቄዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚፈጸሙም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
