የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት አብዲራህማን አብዲላሂ፣ የግዛቲቷ ጸጥታ ኃይሎች ለኢትዮጵያዊያን የተለየ ጥበቃ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የግዛቲቷ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
ፕሬዝደንቱ ይህን ትዕዛዝ የሠጡት፣ ሰሞኑን ሐርጌሳ ውስጥ በአንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ላይ የተወሰኑ ግለሰቦች ማስፈራሪያና ዛቻ ሲያደርሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል መሠራጨቱን ተከትሎ ነው።
ፕሬዝዳንቱ፣ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ሥር የሰደደ ግንኙነት እንዳላት መናገራቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።
የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ ተከትሎ፣ ጸጥታ ኃይሎች አብዲሪሳቅ ሙሴ የተባለ በቲክቶክ ላይ በተለይ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች የጥቃት ሰለባ እንዲኾኑ ሲቀሰቅስ ነበር የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውለዋል መባሉን ዋዜማ ዘግባለች።
