የቂሊንጦ ማረፊያ ማእከል መያዝ ከሚችለው በላይ የያዘ በመሆኑ ከፍተኛ መጨናነቅ ተፈጥሯል

Date:

የቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል መያዝ ከሚችለው የተጠርጣሪዎች ቁጥር በላይ የያዘ በመሆኑ ከፍተኛ መጨናነቅ መፈጠሩን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ገለጸ። በሌላ በኩል በማዕከሉ ተጠርጣሪዎች ስለሚኖራቸው ቆይታ እና ስለሚያገኟቸው አገልግሎቶች በቂ ማብራሪያ የሚሰጣቸው መሆኑ አበረታች ከሆኑ ሁኔታዎች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ታኅሣሥ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል ጉብኝት ማድረጉን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በዚህም የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ በታዩ መልካም ለውጦች እና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ከተጠርጣሪዎች ተወካዮች፣ ከማእከሉ እና ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውቋል።

በጉብኝቱም ማዕከሉ መያዝ ከሚችለው የተጠርጣሪዎች ቁጥር በላይ የያዘ በመሆኑ ከፍተኛ መጨናነቅ መፈጠሩን ኮሚሽኑ አመላክቷል።

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ተጠርጣሪዎች ከሌሎች ተለይተው አለመያዛቸው፣ መዝጊያ የሌላቸው መጸዳጃ እና መታጠቢያ ቤቶችን ጨምሮ የተወሰኑ የውሃ ቧንቧዎች አገልግሎት ያቆሙ መሆናቸው፣ በማረሚያ ቤቱ የተወሰኑ ዞኖች ለተጠርጣሪዎች በቂ የመንቀሳቀሻ ቦታ አለመኖሩም በማዕከሉ የተገኙ ድክመቶች ሆነው ተለይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች ለመያዝ የሚፈቀድላቸው አነስተኛ የብር መጠን (እስከ 200 ብር ብቻ) መሆኑ የሚያስፈልጓቸውን ሸቀጦች ለመግዛት በቂ አለመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች የሚፈልጓቸውን መጻሕፍት ለማስገባት መቸገራቸው እንዲሁም ለአንድ ተጠርጣሪ የእለት ቀለብ የተመደበው 35 ብር ምግብ ለማቅረብ በቂ አለመሆኑ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ኢሰመኮ በጉብኝቱ ለመገንዘብ መቻሉን ኢሰመኮ ገልጿል።

በሌላ በኩል ተጠርጣሪዎች በማእከሉ ስለሚኖራቸው ቆይታ እና ስለሚያገኟቸው አገልግሎቶች በቂ ማብራሪያ የሚሰጣቸው መሆኑ፣ መብቶች እና ግዴታዎቻቸውን በጽሑፍ እንዲያገኙ መደረጉ፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ መልካም መሻሻል የታየባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ኢሰመኮ አመላክቷል።

ከዚህ በአሻገርም ለሃይማኖት ነጻነት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ፣ በማእከሉ መሠረታዊ ፍጆታዎችን በግዢ ማግኘት የሚቻልበት አማራጭ መቅረቡ እና ለመጠጥና ንጽሕና መጠበቂያ የሚሆን በቂ የውሃ አቅርቦት መኖሩ በጉብኝቱ አበረታች ሆነው ካገኛቸው ሁኔታዎች መካከል መሆናቸውን ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ፍርድ የተሰጣቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ለማዛወር የተላለፈው ውሳኔ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በማእከሉ ለሚገኙ የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች የተመደበው በጀት እንዲሻሻል ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ እንዲሁም ከንጽሕናና ሌሎች አገልግሎቶች መሠረተ ልማት መሟላት ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና የቂሊንጦ ጊዜ ቀጠሮ ማረፊያ ማእከል የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የአሁኑን ጉብኝት ጨምሮ ኢሰመኮ በየጊዜው የሚያካሂዳቸው የክትትልና ውትወታ ተግባራት የተጠርጣሪዎችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል ጠቃሚ ግብአት እንደሚሆናቸው በመጠቆም ተቋማቱ ተቀራርበው መሥራታቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢሰመኮ የተመለከተው የማዕከሉን መጨናነቅ በተመለከተም ችግሩን ለመቅረፍ ፍርድ የተሰጣቸውን ሰዎች ወደ ቃሊቲ ከፍተኛ ማረሚያ ተቋም ለማዛወር በማረሚያ ቤቱ የተወሰነ መሆኑን፤ የታራሚዎች የእለት በጀት የሚሻሻልበትን ሁኔታ በተመለከተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሚገኙ እንዲሁም ተጠርጣሪዎች በቆይታቸው ለመሠረታዊ ፍላጎት ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ሊያደርጉ የሚችሉበትን ሥርዓት ለመፍጠር ከባንኮች ጋር እየተሠራ የሚገኝ መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ10 ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ጥቅምት 12 ቀን 2019...

ዳሸን ባንክ እና ሼባ ማይልስ የፕላቲንየም ብራንድ የማስተር ካርድ ይፋ አደረጉ

ዳሸን ባንክ እና ሼባ ማይልስ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ደንበኞች የፕሪሚየም...

የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊ ኢራንን አስጠነቀቁ

ቡሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ጄይ ክላይተን አርብ ዕለት ኢራን በውጭ...

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ  በአመት ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታጣለች

85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርናው ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን...