በ2017 ዓ.ም የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በጋሞና አካባቢው ዞኖች ሀገረ ስብከት በቁጫ ወረዳ ያጋራ ቀበሌ የቃል ኪዳኑን ታቦት እና የእምነቱን ሥርዓት በሚያቃልል መልኩ በቲክቶክ (TikTok) ምስልና ቪዲዮ ሲያሰራጩ የነበሩ ግለሰቦች የፍርድ ውሳኔ ተላለፈባቸው።
ሕዝቅኤል ማጃ እና መርዶክዮስ ማጃ የተባሉ ግለሰቦች የሃይማኖትን ሰላምና ስሜት በመንካት (በ1997 የወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 492(ለ) መሠረት) የቁጫ ወረዳ ፍርድ ቤት ባቀረበው የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ተከሳሾቹ ጥፋታቸውን መከላከል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ በ 1 ዓመት ቀላል እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
የጋሞና አካባቢው ዞኖች ሀገረ ስብከት እንደገለጸው ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ሰባኪ እና ይቅር ባይ ብትሆንም፣ እንዲህ አይነት ፀያፍ ድርጊቶች በሕግ አግባብ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጽዋል። ይህ ውሳኔ ለሌሎች መሰል ድርጊት ለሚፈጽሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ትምህርት እንደሚሆን አስታውቋል ።
© የጋሞና አካባቢው ዞኖች ሀገረ ስብከት ሚዲያ
