ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ማክሰኛ ሰኔ 30 2018 ዓ .ም ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾችን የተወሰኑትን አንደሚከተለዉ አቅርበናል።
የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ “አሸናፊ እና ተሸናፊ እኩል ቁጭ ብለው የተደራደሩበት ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በትግራይ ወጣቶች “በጉልበት ታፍሰው ወደ ሱዳን ጦርነት ተወስደዋል” ያሉት ዐቢይ “በማያውቁት ጉዳይ ሕይወታቸውን እያጡ ነው” ብለዋል።
አያይዘውም የትግራይ ሕዝብ በክልሉ ካለው አንጻር “በደሴ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር. . .” በሰላም ወጥቶ መግባት ይችላል ብለዋል።
ይሄንኑ ንጽጽር ለአማራ ክልል እና ለኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ተጠቅመው “ዜጎች በገዛ ቀዬአቸው እየታመሱ ነው” ብለዋል።
“ከቀዬ ሸሽቶ መኖር የተሻለ ሰላም የሚሰጥ” ሆኗል ሲሉ አክለዋል።
“ትግራዋይ እና ኢትዮጵያዊ የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ ሆኗል” ሲሉም የሚስተዋለውን አለመረጋጋት ገልጸዋል።
ተፎካካሪዎች “በነፃነት እንዲያሸንፉ” 15 በመቶ ወንበሮችን ተለቅቋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ “ታይቶ የማይታወቅ” በሚል አሞካሽተውታል። በዘንድሮው ምርጫ ፓርቲያቸው ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ አግኝቶ ያሸነፈ ሲሆን፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች “ተጭበረበረ ወይም መንግሥት በኃይል ወሰደ በማይሉበት ሁኔታ ብቻቸውን ይወዳደሩ” ብለው 15 በመቶ በሚሆኑ ወንበሮች እንደለቀቁ አስታውቀዋል።
በ85 በመቶ ወንበሮች አለመወዳደራቸውን “ለዲሞክራሲ ቀናኢነት” ሲባል የተደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በፓርላማ 15 በመቶ አልወዳደርም የሚል ፓርቲ በድፍን አፍሪካ መኖሩን እጠራጠራለሁ” ሲሉ ዮፓርቲያቸውን ውሳኔ አሞካሽተዋል።
“ብዙ ድምፆች እንዲገቡ ፍላጎት ነበር፤ ብዙ ሰዎች እንዲሳተፉ ፍላጎት ነበር” ሲሉ ገዢው ፓርቲ በፈቃደኝነት ወንበር መልቀቃቸውን ምክንያት አድርገው አቅርበዋል።
ፓርቲያቸው ሳይፎካከራቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወዳደርረው እንዲያሸንፉ የተነደፈውን እቅድ “ወጣ ያለ ውሳኔ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሉታዊ ጎኑ ሳይሆን በአዎንታዊ መልኩ “ታይቶ አይታወቅም” ብለዋል።
“15 በመቶ [ወንበር] ይቅርብን ያልነው ጉዳይ ብዙ ድምፅ ለመስማት ስለሆነ የብልፅግና ፓርቲ አባላት እንደዚህ ባለው ወጣ ያለ ውሳኔ አካል በመሆናችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል” ብለዋል።
ግጭቶችን በተመለከተ
ግጭትን በተመለከተ- ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአገሪቱ የሚስተዋሉ ግጭቶች እና ሰላም ማጣትን በተመለከተ የተነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ “ታፍነው የቆዩ” ያሏቸው ችግሮች በማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት እንዲሁም በሌሎችም ምክንያቶች መስፋፋቱን ጠቅሰዋል።
ነገር ግን አሁን ላይ “በሕዝብ እና ሕዝብ” “በሃይማኖት እና ሃይማኖት” መካከል የሚስተዋል ግጭት “እንደቀነሰ” ተናግረው ግጭቶች “በብሔር መካከል” መሆናቸውን ተናግረዋል።
በድርድር ወደ ሰላም የተመለሱ እንዳሉ ሁሉ “የተቀሩትም ይመለሳሉ” ብለው እንደሚያኑ ገልጸዋል።
ብልፅግና ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ አለመቆየት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ “ምርጫው ዒላማ ሆኖ ነበር” ብለዋል።
ሕዝቡ “ጥይት ሳይፈራ” ድምጽ እንደሰጠ ጠቅሰው፤ ምርጫውን ስላሸነፈው ፓርቲያቸው ብልጽግና ሲናገሩም “15 በመቶ አልወዳደርም የሚል ፓርቲ እንደሌለ” ተናግረዋል።
ገዢ ፓርቲ ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ እንዳይቆይ ማድረግን እንደሚደግፉ አክለዋል።
“መቋቋም፣ መጠቀም፣ መግራት”
ጠቅላይ ሚኒስሩ የውጭ አገር ግንኙነትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያላት መርኅ “መቋቋም፣ መጠቀም፣ መግራት ነው” ብለዋል።
የአገሪቷን “የውሳኔ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ” ግባቸው እንደሆነ የተናገሩት ዐቢይ፣ መቋቋም አገር እና ተቋም መፍጠር መሆኑን፣ መጠቀም ፈተናን ወደ ዕድል መቀየር መሆንን እና መግራት “በሰው አጀንዳ ከመገራት የራስን አጀንዳ ፈጥሮ በመግራት” መርኅ እንደሚመሩ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል “ጠላት” የሚከተለው ያሉት መካድ፣ መርሳት እና ምኞት ነው። ኢትዮጵያ በቀላሉ እንደማትበገር መካድ፣ የኢትዮጵያ ራሷን መከላከል እንደምትችል መርሳት እና ያለፈ ስልት እስረኛ የመሆን ምኞት እንዳለ ገልጸዋል።
“የትምህርት ዘርፍን ከየትኛውም ዘርፍ በላይ እንኮራበታለን”
በብሔራዊ ፈተና የሚወድቁ ተማሪዎች መበራከት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ ከተነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን “በጣም የተሳካልን የሥራ መስክ የትምህርት ሚኒስቴር ነው” ብለዋል። የትምህርት ዘርፍን “ከየትኛውም ዘርፍ በላይ እንኮራበታለን” ሲሉም ተናግረዋል።
በሰባት ዓመታት 35 ሺህ መዋዕለ ሕጻናት መገንባታቸውን እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል። እነዚህ ሕጻናት “ምርጫ አይመርጡንም፣ ፌስቡክ ላይክ አያደርጉንም. . . በ20 ዓመት የኢትዮጵያ ሕልውና ናቸው” ብለው የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንዳላቸው አስረድረዋል።
“ከአርሲው ግድያ ጋር በተያያዘ “
“ኢትዮጵያ የሃይማኖት አገር ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርሲ የተፈጸመው ግድያ “ሃይማኖታዊ ገጽታ” እንደሌለው አስረግጠው ተናግረዋል።
“በሃይማኖት እና ብሔር ጥላ ሥር አየወደቀ” በማለትም የተለያዩ ፍላጎቶች ከጀርባው መኖራቸውን አመላክተዋል። “አዲስ አበባ ተቀምጠው ቤንዚን እያርከፈከፉ. . . እሳቱን ያቀጣጥላሉ” አሉ ሲሉም ከስሰዋል።
በአርሲ የተፈጠረው “ምርጫውን ከማደናቀፍ ሙከራ” ጋር አያይዘው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃይማኖት ተቋማት “ቦምብ እና ክላሽ ስንይዝ ነበር” ብለዋል።
“. . . ያቃታቸው ኃይሎች ሕዝብን ሊያጠቁ አንድ መንደር ሄዱ አርሲ ውስጥ። ሕዝብ የሚያጠቃ እና የሚከላከል ኃይል ተጋጠመ” በማለት በክስተቱ ከሞቱት 11 ሰዎች 8ቱ ሚሊሻ መሆናቸውን ጠቅሰው “ሕይወታቸውን ገብረው ለንጹኃን ሕይወት የተጎዱ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ክስተቱን “የሃይማኖት መልክ ለመስጠት ታስቦ ነበር” ብለውም በጥቃቱ ሙስሊሞችም መገደላቸውን እና 22 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።
‘ትንኮሳ መከላከል የሚችል ቁመና ’
የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ቀውስ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታውን “የመጥረቢያ ፖለቲካ ሰለባ” ሲሉ ገልፀውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት “የሻዕቢያን” ተልዕኮ እያስፈፀመ ያለ፤ ‘የራሱ ዓላማ የሌለው’ “መጥረቢያ” ነው ሲሉ ከስሰዋል።
“ኢትዮጵያ የሰላሟ መድፍረስ ምንጭ የት እንደሆነ ስለምናውቅ ከምንጩ የሚነሳው ማንኛውንም ትንኮሳ መከላከል የሚችል ቁመና በመፍጠር ላይ የምንገኝ መሆኑን ለተከበረው ምክር ቤት መግለፅ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገሪቱን አንድነት እና ሉዓዊነት አደጋ ውስጥ የሚያስገባ “ማንኛውም ነገር ከመጣ” መከላከል የሚያችል ቁመና አለን ብለዋል።
የውጭ ተልዕኮ አስፈፃሚ ብለው ያመለከቷቸው የአገር ውስጥ ኃይሎችን “ጉዳቱ የጋራ ስለሚሆን…መታገስ እና ማስተማር” ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል።
“እንኳን ሻዕቢያ፣ ወያኔ እና ሱዳን ሌላም ቢጨመር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት የለውም”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደርግ መንግሥት በወደቀበት “ስሌት” መንግሥታቸውን ለመጣል የሚያስቡ ኃይሎች ስጋት እንደማያሳድሩ ገልፀው፤ አሰላለፋቸውንም “ምኞት” ብለውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ኃይሎች “መከላከል የሚያስችል ብቃት እየገነባን ነው ያለነው” ብለዋል።
“ሰዎች ባረጀ ባፈጀ ስልት፤ ድሮ በሠራ ስልት አሁን ለመጠቀም መሞከር ጠቃሚ አይደለም” ያሉት ዐቢይ፤ ለዚህም የሰጡት ምክንያት ራሱን በድሎ የሚዋጋ ኃይል የለም የሚል ነው።
“ጊዜው ተቀይሯል” ብለዋል።
“ሀብት እያፈራህ፤ ሀብትን እያጣጣምክ ራስን ደግሞ ለመስዋዕትነት ማዘጋጀት አብሮ አይሄድም። አልፎበታል። ይህ ምኞት አይጠቅምም።”
በትግራይ ክልል ጦርነቱ እንዲፈነዳ “ሰፊ ፍላጎት” አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እምቢ ያልንበት ምክንያት ትርፍ የለውም ብለን ነው” ብለዋል።
“እንኳን ሻዕቢያ፣ ወያኔ እና ሱዳን ሌላም ቢጨመር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት የለውም” ብለዋል።
ህወሓት 50 ዓመት የቆየ “አንጋፋ ፓርቲ ሆኖ ወጣቱን ማመን” አመቻሉን በንግግራቸው ጠቅሰው “ድል እና ህወሓት አራንባ እና ቆቦ” ናቸው ሲሉም አጣጥለዋል።
አሁን ያለውን የአዲስ ትውልድ አስተሳሰብ እና አቅጣጫ አለመቀበል “የትም አያደርስም” ሲሉም ተናግረዋል።
ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ 40 ምንጭ. . . እና ሌሎችም ከተሞች በመጥቀስ “ኮሪደር ልማት በመቀለ ማየት ነው ምኞታችን ከዛ ውጭ ያለውን አንፈልግም” ብለዋል።
ስለ ህወሓት የሰጡት አስተያየት ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በማንሳት የሕዝቡ ያለው የትግል ሚና እንዳማይካድ ጠቅሰው “አሁን ያለው የተለየ ነው” ሲሉ የሁኔታዎችን መለወጥ ተናግረዋል።
“ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ. . . ለመነጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ “ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ፣ አእምሮ ከገዛ ለመነጋገር፣ ሰላም ለማምጣት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።
አያይዘውም “ከሰላም ውጪ ያለው አይጠቅመንም” ሲሉም አክለዋል። በቀጣይ ዓመት በሚቋቋመው አዲስ ምክር ቤት ውስጥ የማይኖሩትን የሕዝብ እንደራሴዎች ባለፉት አምስት ዓመታት አስተዋጽኦቸው ምሥጋና አቅርበዋል።
የብልጽግና አባል የሆኑም ያልሆኑም የምክር ቤት አባላትን “ኢትዮጵያም መንግሥታችንም አብዝቶ ያመሰግናችኋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት “ብርቱ ሰዎች፣ ሐሳባችሁን ለመግለጽ የደፈራችሁ፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሞከራችሁ፣ ሐሳባችሁ ምንም ይሁን ምንም በግልጽነት የገለጻችሁ ጀግኖች ናችሁ” በማለትም አክለዋል።
ዛሬ የመጨረሻ ስብሰባውን ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመኑን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት መስከረም ማብቂያ ላይ አዲሱ ምክር ቤት ይተካል።
”በቀጣይ 5 ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች እንገነባለን”
የቤት ጉዳይን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በቀጣይ 5 ዓመታት ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ቤቶች እንገነባለን” ብለዋል።
በመንግሥት፣ በግል፣ በመንግሥት እና በግል ዘርፍ ጥምረት የቤት ግንባታ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።
ለዚህም የሦስት አውታር (3ዲ) ቴክኖሎጂን ጨምሮ የግንባታ ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካዎች መስፋፋት ያለውን አስተዋጽኦ ተናግረዋል።
የቤት ዘርፍ በሥራ ፈጠራ እና የምጣኔ ሃብት ማነቃቃት ያለውን ሚና አንስተዋል። ከሥራው ዘርፍ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ 13%፣ በውጭ አገራት 27% ዕድገት መኖሩን ጠቅሰው “5 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ አስይዘናል” ብለዋል።
“በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት”
የኢንዱስትሪው ዘርፍ “ከለውጡ በፊት ከነበረበት 47% የማምረት አቅም ዛሬ ወደ 67% መድረሱን” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።
የማዕድን ዘርፍ 24% ዕድገት፣ የኢነርጂ ዘርፍ 23% ዕድገት፣ የአገልግሎት ዘርፍ 9.8% ዕድገት እንዳለ ጠቅሰዋል። ይህም ኢትዮጵያ 10.3 ማደግ እንደምትችል ያመለክታል ብለው ይህም “በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት ነው” ብለዋል።
ጨምረውም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያላት ሪዘርቭ (ተቀማጭ ገንዘብ) ከ20 አጥፍ በላይ አድጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አገሪቱ “የመቋቋም አቅሟ” ማደጉን በመጥቀስም “ኢትዮጵያ ከተፈጠረች ወዲህ ያለ ሪዘርቭ የአሁኑ በእጥፍ ይበልጣል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ገቢ በ27 ዓመት 1 ትሪሊዮን ዶላር የነበረ መሆኑን በመጥቀስም፣ ዘንድሮ ከ1.5 ዶላር በላይ መድረሱን አመለክተዋል።
“የ17 ዓመቱን በአንድ ዓመት ማምጣት ዕድገት ካልሆነ ምን ዕድገት ይሆናል?”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት በተመለከተ በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት “ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ” መሆኑን ተናግረዋል።
“የ17 ዓመቱን በአንድ ዓመት ማምጣት ዕድገት ካልሆነ ምን ዕድገት ይሆናል?” ሲሉ ለውጡን በንጽጽር ገልጸዋል። 38 ቢሊዮን ዶላር የውጭ አገር ካፒታል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በ17 ዓመታት ከቡና ኤክስፖርት ያገኘችው 3.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ጠቅሰው፤ አሁን ግን በአንድ ዓመት 3.1 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት መደረጉን ተናግረዋል።
ወርቅ በ27 ዓመት 3.7 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት እንደተደረገ እና አሁን ግን የወርቅ የውጭ ንግድ በአንድ ዓመት 5.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።
