ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና ያለውን በማካፈል መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትአስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ለመላው የእስልምና ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል አደረሳችሁ ሲል መልዕክት አስተላልፏል።
ኢድ አል አድሃ የመተሳሰብ በዓል ነው ያሉት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼይኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ፤ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብና ያለውን በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስገንዝበዋል።
በእስልምና አስተምሮ መሰረት የአረፋ ቀን ዋጋዋ ትልቅ በመሆኗ መላው ህዝበ ሙስሊም በጾምና በዱዓ (በጸሎት) እንዲያሳልፉ ሼይኽ ሐጂ ኢብራሒም መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
እርድ ማከናወን ለማይችሉ አቅመ ደካሞችንና አሳዳጊ የሌላቸውን ህጻናት እንዲሁም ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖችን ሁሉ አቅም በፈቀደ መጠን በመደገፍ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያየ እምነት ተከታይ ለበርካታ ዘመናት ተዋዶና ተከባብሮ የኖረባት ሀገር እንደመሆኗ ምዕመኑ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር አንድነቱንና ወንድማማችነቱን ይበልጥ በማጠናከር በዓሉን ማሳለፍ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
