የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረጅም ርቀት ጉዞዎች የሚውሉ ዘጠኝ 787-9 ድሪምላይነር ጄት አውሮፕላኖችን ከአሜሪካው የአውሮፕላን አምራች ቦይግን ለመግዛት ትዕዛዝ ሰጠ።
በአፍሪካ ቀዳሚው አየር ትራንስፖርት አቅራቢ ኩባንያ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ጥያቄው መቅረቡን አስታውቀዋል። አውሮፕላኖቹ ተገንብተው ከአውሮፓውያኑ 2034 አስከ 2033 ባለው ጊዜ ውስጥ የሚቀርቡ ይሆናል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እነዚህ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ለመግዛት ትዕዛዝ ያቀረበው በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ያሉትን 145 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ለማስፋት ባለው ዕቅድ እንደሆነ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው “ዘላቂ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት ባለን ስትራቴጂያዊ ራዕይ ምክንያት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን መግዛታችንን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማችንን እንቀጥላለን” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አየር መንገዱ ከወራት በፊት ዱባይ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ትዕይንት ወቅት 11 ቦይንግ ማክስ 737 ጄት አውሮፕላኖች ግዢን መፈጸሙ ይታወሳል።
በተከታታይ ዓመታት በአፍሪካ ቁጥር አንድ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻዎቹን በማስፋት በየጊዜው የአውሮፕላኖቹን ቁጥር እያሰፋ ነው።
ከሳምንት በፊትም በአፍሪካ ትልቁ የተባለው አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ሥራውን ጀምሯል።
