የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በዲጂታል ኢቢሲ ምረቃ ስነስርአት ላይ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የልማት ስራ ስኬት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በከተሞች በኮሪደር ልማት አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች ያሉት ሚኒስትሩ ላለፉት ሰባት አመታት አለም አቀፋዊ ተፅእኖ መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባቱን ገልጸዋል ።
በማህበራዊ ዘርፍም የሰለጠነ የሰው ሀይል እና በበጎነት መርህ መልካም ዜጋ በማፍራት ረገድ ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል ። በሜጋ ፕሮጀክቶች ረገድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃት ከቀናት በኋላ እንደሚከናወን ጠቁመዋል ።
ዶ/ር ለገሰ የባህር በር ተጠቃሚነትን በሚመለከትም የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጉዞ ከግማሽ መንገድ በላይ መራመዱን አስታውቀዋል ።
ኢትዮጵያ በሁሉም እንቅስቃሴዎች እያገኘች ያለውን ጉልህ ስፍራ ለማስተጓጐል ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከሚዘውሯቸው የውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ፈተና ተከፍቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ገፅታ ለማጠልሸት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን በዲጂታል ምህዳር በመተባበር የመመከት ስራ እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሩ አመላክተዋል ።
ዶ/ር ለገሰ ግጭት እና ብጥብጥን የኢትዮጵያ ማዳከሚያ ስልት አድርገው የሚጠቀሙ ሀይሎችን አላማ በመረዳት ዜጎችም የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።
በቤተልሔም ገረመው
