ኢንተርፖል ለ196 ሀገራት ከሚሰጣቸው የፖሊስ ኃይል ስልጠናዎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ከመግባባት ላይ መደረሱ ተገለጸ
የዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) በቀጣይ በትምህርትና ስልጠና በተለይም በቴክኖሎጂ የሚጠቀም ፕሮፌሽናል የፖሊስ ኃይል ለመፍጠር ለ196 ሀገራት ከሚሰጣቸው የፖሊስ ኃይል ስልጠናዎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ከመግባባት ላይ መደረሱን ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የኢንተርፖል ፕሬዚዳንት ሜጀር ጀነራል ዶ/ር አህመድ ናስር አል ራኢሲን ትናንት ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሽብርተኝነትን፣ ሕገ- ወጥ የሰዎች፣ የጦር መሣሪያ እና የአደገኛ ዕፅ ዝውውርን እንዲሁም ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል መወያየታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የኢንተርፖል ፕሬዝደንት ጥሪያቸውን ተቀብለው ኢትዮጵያን በመጎብኘታቸው ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ኢንተርፖል በትምህርትና ስልጠና በተለይም በቴክኖሎጂ የሚጠቀም ፕሮፌሽናል የፖሊስ ኃይል ለመፍጠር ለ196 ሀገራት ከሚሰጣቸው የፖሊስ ኃይል ስልጠናዎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ከመግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
