ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአዘዞ ቁጥር 2 መምህራን መኖሪያ ኮንዶሚኒየም መንደር ውስጥ አዲስ የማህበረሰብ ትምህርት ቤት አስገንብቶ አገልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ። ይህ ትምህርት ቤት የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የሆስፒታል ሐኪሞች፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ሰራተኞች ልጆች ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩበት ነው።
ፕሮጀክቱ የዩኒቨርሲቲው ሰሞኑን ካስመረቃቸው 22 ኘሮጀክቶች አንዱ ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲው ሰራተኞች በአካባቢው ተረጋግተው እንዲቆዩ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።
ትምህርት ቤቱ 10 የቅድመ መደበኛ ክፍሎችን የያዘ ህንፃ እና 28 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ አራት ወለል ህንፃ ያካተተ ሲሆን፣ ደረጃውን የጠበቀ መደበኛ ትምህርት ይሰጣል።
ይህ ተነሳሽነት ለዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር በተጨማሪ በአካባቢው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
