የጤና ሚኒስቴር በገጠራማው የሀገራችን ክፍሎች የሚታየውን የሕክምና አቅርቦት ችግር ለመቅረፍና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ 1,183 የሞተር ሳይክሎች እና 380 የሶላር የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ድጋፍ አበረከተ።
በተካሄደው የርክክብ መርሃ ግብር ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ደባ እንደገለጹት፤ ድጋፉ በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ተቋማት የሚታየውን የአገልግሎት መቆራረጥ ለመፍታት ያለመ ነው።
በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙትና በፀሐይ ኃይል የሚሰሩት ሞተር ሳይክሎች የጤና ባለሙያዎች በፍጥነት ተንቀሳቅሰው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ ሲሆን፤ ከዩኒሴፍ እና ከጋቪ የተገኙት የሶላር ኃይል አቅርቦቶች ደግሞ የኤሌክትሪክ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ለሕክምና መሣሪያዎች አስተማማኝ ምንጭ ይሆናሉ።
ይህ ተግባር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ሁሉን አቀፍ፣ ጥራት ያለውና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አካል መሆኑ ተገልጿል።
