የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ሰይፈ ጀማል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የወለኔ አርሶ አደሮች የዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ የነበረ ሕዝባዊ ጉዳይ ነው።
ፓርቲው ካሉት አባላት ከ85 በመቶ በላይ አርሶ አደሮች ናቸው። ይህ ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2013 ዓ.ም ጊዜያዊ እውቅና የተሰጠው ቢሆንም እስከዛሬ ድረስ ግን ሙሉ የእውቅና ምስክር ወረቀት ሊሰጠው አልቻለም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
አቶ ሰይፈ፤ ፓርቲውን ሲመሠርቱ የቀድሞው ፓርቲ ማለትም የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ወሕዴፓ) ውስጥ አባል እንደነበሩ አስታውሰዋል። ለእኛ ምን እንደሆነ በግልጽ በማናውቀው መንገድ ለዓመታት እውቅና ሳናገኝ ተጉላልተናል ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ሙሉ የእውቅና የምስክር ወረቀት ለማግኘትም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለጉዳዩ በተጠየቀበት ወቅት በሰጠው የጽሑፍ ምላሽ እንዳብራራው፤ እነአቶ ሰይፈ ጀማል የወለኔ አርሶ አደሮች ኅብረት ፓርቲ (ወአህፓ) አደራጅ ኮሚቴ መጋቢት 4 ቀን 2015ዓ.ም የፓርቲውን መሥራች ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ ቦርዱ ጉባዔውን እና በጉባዔው የተላለፉ ውሳኔዎችን በማጽደቅ ዕውቅና እንዲሰጠው ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል።
ቦርዱም አመልካች ፓርቲው ያቀረባቸውን ሠነዶች፤ የቦርዱ ታዛቢዎች ያቀረቡትን ሪፖርት ከአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንጻር መርምሯል።
የወለኔ አርሶ አደሮች ኅብረት ፓርቲ ምልዓተ ጉባዔ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 5 (1) ላይ 207 አባላት እንደሆነ ቢገለጽም፤ ፓርቲው መሥራች ጉባዔውን በሚያካሂድ ጊዜ በቦርዱ ታዛቢዎች ተቆጥሮ የተረጋገጠው 86 ጉባዔተኛ ብቻ ነው ብሏል።
ይህም በመተዳደሪያ ደንቡ እና በምርጫ አዋጁ ከተቀመጠው የምልዓተ – ጉባዔ ቁጥር የሚያንስ በመሆኑ ፓርቲው ያደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ተቀባይነት እንዳያገኝ ካደረጉ ምክንያት አንዱ መሆኑን ገልጿል።
ከአዋጅ ቁጥር 1162/11 እና ከጉባዔው ተሣታፊዎች አንጻርም ሲታይ የፓርቲው ሰብሳቢ አባል ያልሆኑ ግለሰቦች በስብሰባው እንዲካፈሉ መደረጉ፤ ጉባዔተኛው እየፈረመና እየተመዘገበ ወደ አዳራሹ እንዲገባ ባልተደረገበት ሁኔታ የአመልካች ሰብሳቢ አስቀድሞ የተዘጋጀ የተፈረመ ሠነድ ይዘው መገኘታቸው እና ይህንንም ለቦርዱ በማቅረብ ምልዓተ – ጉባዔ እንደተሟላ ተደርጎ መቅረቡን ቦርዱ አስረድቷል።
ፓርቲው የዕውቅና የምሥክር ወረቀት ሊሰጠው ያልቻለው የመሥራች ጉባዔውን በማከናወን ለቦርዱ መረጃ በሚሰጥበት ጊዜ በፈጸማቸው የሕግ ጥሰቶች፤ እንዲሁም በተፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ምክንያት በአዋጅ ቁጥር 1162 /2011 አንቀጽ 64/5 እና 65/4/ መሠረት ፓርቲው ያቀረበውን የምዝገባ ማመልከቻ ውድቅ ማድረጉን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
