(በእወቀተ ስዩም)
የግእዝ ፊደላትን ረቂቅ የቀረጹልን የአክሱም ሊቃውንት ናቸው፤ ምናልባት ከክርስቶስ ልደት በፊት ሳይሆን አይቀርም፤ ይሁን እንጂ፤ ፊደሎችን አራብታ ፤ ቅጥያ አበጅታ ትልልቅ ሀሳብ መግለጽ እንዲችል አድርጋ ያደራጀችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ቤተክርስትያን ናት፤ እንዲህ ቅሽር ያለ፤ የዘነጠ፤ ፊደል ስላወረሰችኝ አመሰግናታለሁ፤
ስእል መሳል፥ ድርሰት መጻፍ፤ ቅኔ መቀኘት ፤ ዜማ ማዜም፤ ዘመን መቀመር፤ ታሪክ መመዝገብ እኒህ ሁሉ የቤተክስያን ወርሶች ናቸው፤
ሰውን ሰው ያደረገው ታሪክ አይደለም እንዴ ?! ገበሬን ከበሬ የሚለየው ትውስታ ነው፤ በዚህ ረገድ ካየነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የታሪክ መዝግብ ብቻ አይደለችም፤ ህያው ሙዝየም ናት ፤ ሙዝየም የቀደምቶቻችን የእጅ እና የአእምሮ ውጤቶች የሚገኙበት ቤት ነው፤ አንድ ሺህ አመታት ያስቆጠረ ጽናጽል ብሪትሽ ሙዝየም ውስጥ ልታገኝ ትችላለህ፤ ይሁን እንጂ ጽናጽሉ እንዴት እንደሚሰራ ሙዝየሙ አይነግርህም፤ እንዲህ ያለው እውቀት ሙዝየም በመጎብኘት ወይም መጻህፍትን በማየት አይገኝም፤ ይህንን የምታውቀው ባጥቢያህ ወደ ሚገኝ ደብር ጎራ ስትል ነው፤ ቤተክርስትያን ውስጥ ነባር ቅርሶች ብቻ ሳይሆኑ ነባር ተሰጥኦዎች ካንዱ ትውልድ ወደ አንዱ ትውልድ ይሸጋገራሉ፤
ምእራቡ አለም እውቀት የማከማቸት ባህል አለው፤ ግን አንዳንዴ የእውቀት ፍለጋው ክፍተት ያጋጥመዋል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ቤተክርስትያን እንዲህ ዓይነቱን ክፍተት Missing link በመሙላት የአገር ኩራት ምልክት ሆና ቆይታለች፤ የመጽሀፈ ሄኖክን ታሪክ የሚያውቁ የማወራው ይገባቸዋል፤
ከግሪክ ስልጣኔ መክሰም በሁዋላ አብዛኛው የምእራብ ዓለም ቅድስና የሚለውን ጸጋ የሚያቀዳጀው ለወንዶች ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ግን ለሴት ቅድስታት እና ሰማእታት እውቅና ሰጥታለች፤ ገድል እና ድርሳንም ትጽፍላቸዋለች፤ በቅድስና ትርጓሜው ላይ ላንስማማ ልንከራከር እንችላለን፤ ያም ሆኖ፤ ሴትን ” አሳሳች” እና ” የሀጥያት ሰበብ” ብቻ አድርጎ ከሚያቀርበው ትውፊት የተለየ ትውፊት ማቅረብ ስልጣኔ ነው፤
በአገራችን ፤ በኩራት ለጎብኝዎች ከምናቀርባቸው ድንቆች መካከል ግንባርቀደሞቹ የላሊበላ አብያተክርስትያናት ናቸው፤ ሮሀ ላይ ከተከመሩት ግዙፍ አለቶች መሀል እንዲህ አይነት ውብ ህንጻ አስፈለፍላለሁ ብሎ ለማሰብ በመለኮታዊ ተአምር ማመን የሚጠይቅ ይመስለኛል፤
ያለ ግብዝነት የምናወራ ከሆነ፥ ራሴን እንደ ዓለማዊ እና እንደመርማሪ ነው የማየው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የማመንን ብቻ ሳይሆን የመጠየቅን የመመራመርን ጸጋ አውርሳናለች፤ ከእለታት አንድ ቀን ብራና ላይ የተጻፈ የጥንት የዘፍጥረትን ትርጉዋሜ ሳነብ፥ ስለ ሳጥናኤል አመጽ የሚወሳ ሐተታ አገኘሁ ፤ ሳጥናኤል በፈጣሪ ላይ ማመጹን ተከትሎ የተወሰኑት መላእከት ከሳጥናኤል ጋራ ወገኑ፤ የተወሰኑት በእምነታቸው ጸኑ ፤ የተወሰኑት ደግሞ ፈዘዙ፤
ሊቁ ፥ የፈዘዙትን መላእክት በማስመልከት የጻፈው ሀሳብ አሰላሳይነትን (Freethinking )የሚያበረታታ ደንቅ ሀይለቃል ስለሆነ እንደሚከተለው እጠቅሰዋለሁ፤
“ በሰጣቸው አእምሮ ባይመረምሩበት እዳ ሆነባቸው፤ ዛሬም ሰው በተሰጠው አእምሮ ባይመረምርበት እዳ ይሆንበታል”
