የፓርቲ ተሳታፊዎች በአንድ አጀንዳ ብቻ እንዲሳተፉ የሚገድብ አካሄድ ላይ ጥያቄ ቀረበበት

Date:

የሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊዎች ለውይይት በቡድን እንዲደራጁ የተደረገበት መንገድ ሁሉም የፓርቲ ተሳታፊዎች በአንድ አጀንዳ ብቻ እንዲሳተፉ የሚገድብ በመሆኑ፣ በሁሉም አጀንዳዎች እንዲሳተፉ እንዲደረግ ለኮሚሽኑ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በ8 አጀንዳዎች ለመምከር በዋናው ጉባዔ የሚቀመጡ 4 ሺሕ ተሳታፊዎች በ8 ቡድኖች ተከፋፍለው አንድ ቡድን በአንድ አጀንዳ እንደሚመክር ከዚህ ቀደም ሲገልጽ የነበረ ኮሚሽኑ በዚህ መሰረት መደባ ቢያደርግም፣ ተሳታፊ ፓርቲዎች ግን ይህንን አልተቀበሉትም።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ን ወክለው በሀገራዊ ጉባዔው እየተሳተፉ ያገኘናቸው አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በሰጡን ቃል፣ የፓርቲ ተሳታፊዎች ለምክክሩ ቡድን የተደራጁበት መንገድ የሌለበት ነው በሚል ጥያቄ ማስነሳቱን ገልጸዋል።

“ለምሳሌ ከኢዜማ የተወከልነው አራት ተሳታፊዎች ሁላችንም አንድ አጀንዳ ላይ ነው የተወከልነው፤ ይሄ ተገቢ አይደለም” ብለው፣ ከዚህ ይልቅ ተበታትነን በተለያዩ አጀንዳዎች ብንሳተፍ የሌሎችን ሀሳብ ለማዳመጥ፣ አሉን የምንላቸውን ሀሳቦች ለማካፈል ይጠቅማል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደራጀ ሀሳብ ሰነዶቻቸውን ለኮሚሽኑ በአጀንዳነት እንዳስገቡ አስታውሰው፣ “ከዚህ አንፃር ከፖለቲካ ፓርቲ የመጡትን ተሳታፊዎች ሰብስቦ የአርብቶ አደር አጀንዳ ላይ ብቻ ተወያዩ ቢባሉ ሌሎች ትልልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉባቸው የሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ሳይሳተፉ ይቀሩና ሀሳብ ይጎድላል” ብለዋል።

“ሀሳብ ማዋጣት ሲገባቸው አለማዋጣቱ ብቻ ሳይሆን ጉድለቱ፥ ‘ይህን አጀንዳ አላውቀውም አልተነጋገርኩበትም’ ብሎ በውይይት የተቋጠረውን ነገር እንደገና ወደ መፍታት ውስጥ ሊከት ይችላል” ሲሉም የሚያስከትለውን ተጨማሪ ጉዳት አስረድተዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና አስፈላጊነት የተለያዩ ሀሳቦችን ማቀራረብ፣ የሁሉንም ሀሳብ ማድመጥ ከሆነ የተደራጀ ሀሳብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን “ግድየለም ይሆንን ከተነጋገራችሁ ሌላውን ሌሎች ተነጋግረውላችኋል” ማለቱ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የፓርቲ ተሳታፊዎችን አንድ አጀንዳ ላይ ብቻ ተወያዩ መባሉ ተቃውሞ እንደገጠመው የገለጸው፣ ሌላኛው የቅማንት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አውግቸው ማለደ፣ በኮንቬንሽን ሴንተር ዛሬ በነበረ ውይይት፣ “ሁሉም አጀንዳዎች ላይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እያንዳንዱ አራት ተሳታፊ ተሳትፎ ሊኖር ይገባል” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር ተናግረዋል።

በምክክሩ ለመሳተፍ ድልድሉ ሲሰራ አንድ ቡድን ላይ ከእያንዳንዱ ፓርቲ የተሰጠው ኮታ አራት፣ አራት መሆኑን አስረድተው፣ “ግን አራቱም የፓርቲ ተሳታፊዎች አንድ አጀንዳ ላይ ተደረጉ። ስለዚህ ሁሉም ፓርቲዎች አንድ አጀንዳ ላይ መሆኑ የለባቸውም የሚል ጥያቄ ነው የቀረበው” ብለዋል።

“ሀገራዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ እያንዳንዳችን ሀሳብ ሰጥተን፣ ተመካክረን ነው ሀገራዊ ህግ ሆኖ ሊቀጥል የሚገባው የሚሉ ሀሳቦች ነበሩ። ያን ለማድረግ በፓርቲ ደረጃ ሁሉም ተቋማት በሁሉም ቡድኖች ተከፋፍለዋል” ነው ያሉት። የተነሳው ጥያቄ በኋላ በውይይት ተቀባይነት እንዳገኘ፣ በዚህም ከአንድ ፓርቲ የተመለመሉ አራት ተሳታፊዎች ወደተለያዩ ቦድኖች እንዲበተኑ መወሰኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት “የምንፈልጋቸውን አጀንዳዎች እንዲያዙ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የኢዜማው አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን፣ “ከኮሚሽነሮቹ ጋር ውይይት ተደርጎ ጉዳዩን በዚህ መልኩ አላየነውም ነበር። እንደገና አስተካክለን እንደለድላለን” ማለታቸውን ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በበከሉ ለሚዲያዎች በሰጠው ማብራሪያ ጉዳዩን ለማስተካከል እንደሚሰራ ገልጿል።

በተያያዘ መረጃ፣ ከ4 ሺሕ ተሳታፊዎች መካከል 280 (7%) የሚሆኑት የፖለቲካ ፓርቲ ተሳታፊዎች መሆናቸው ዮሐንስ ገልጸዋል። ባለፉት 50 ዓመታት በዓለም 30 ሀገራዊ ምክክሮች መደረጋቸውን፣ በተሳታፊ ቁጥር ደረጃ የኢትዮጵያው ቀዳሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የብሔራዊ ጉባዔው ተሳታፊዎች ባለፉት ሦስት ቀናት አጀንዳዎቹን እንዴት እናስኪዳቸው በሚል እየተወያዩ እንደሆነና ገና በአጀንዳዎቹ ላይ መመካከር እንዳልጀመሩ ፖርቲዎቹ ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም፣ በስምንት ዋና አጀንዳዎች ሥር ያሉ የሚገኙ ዝርዝር አጀንዳዎችን ለተሳታፊዎች የማሳወቅ ስራ ዛሬ ሲከናውን መዋሉን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጄኤፍኤም 106.7 የሬዲዮ ጣቢያ ለ6 ወራት ታገደ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባደረገው የይዘት ክትትልና የኢንስፔክሽን ምልከታ...

ሱልጣን ቢን ኻሊፋ ግሩፕ በኢትዮጵያ በሆቴል ዘርፍ ሊሰማራ ነው

በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር...

የአሜሪካ የታክስ ህግ የስፔንን የዓለም ዋንጫ ሽልማት ስጋት ላይ ጣለ

የስፔን ብሔራዊ ቡድን ከዓለም ዋንጫ ሊያገኘው ከሚችለው 50 ሚሊዮን...

ህወሓት ከሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ጥምረት አስፈላጊ መሆኑን ገለጸ

ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ...