ትራምፕ የፍጻሜውን ውድድር ይታደማሉ
ፊፋ እሁድ ዕለትበአርጀንቲና እና በስፔን መካከል በሚካሄደው የፍፃሜ ጨዋታ አሸናፊ ለሚሆነው ቡድን የዓለም ዋንጫ ቀለበቶችን እንደሚሸልም ሲገለጽ፣ ዶናልድ ትራምፕም ግጥሚያውን ይታደማሉ ተባለ።
ለአሸናፊ ተጋጣሚዎች ቀለበቶችን መሸለም በአሜሪካ ስፖርት ውስጥ የተለመደ ባህል ነው።
የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ለሚሆነው ቡድን 30 ቀለበቶች የሚቀርቡ ሲሆን፣ በተጨማሪ 1,996 ቀለበቶች ለደጋፊዎች ይሸጣሉ። በእያንዳንዱ ቀለበት ላይ አነስተኛ የዓለም ዋንጫ እና ጽሑፍ ተቀርጾበታል።
ዋንጫውን ለአሸናፊው ቡድን የሚያበረክቱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስካሁን ድረስ ከ102ቱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች መካከል በአንዱም ላይ አልተገኙም።
አሜሪካ በቤልጂየም ተረትታ ከመሰናበቷ በፊት ያደረገቻቸውን ጨዋታዎችንም ቢሆን አልተከታተሉም።
በካናዳ የተከሰተውን ሰደድ እሳት ተከትሎ በኒው ዮርክ የሚኖረው አየር ሊበከል እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
ነገር ግን በሜትላይፍ ስታዲየም የሚካሄደው የፍፃሜ ውድድር ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሚጠቁም ምንም ነገርየለም።
የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ትራምፕ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ እንደሚገኙ አስቀድመው ተናግረው ነበር፤ የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ይህንኑ አረጋግጠዋል።
አሜሪካ ከቦሲኒያ ሄርዜጎቪኒያ ጋር ባደረገችው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ በተቃራኒው ቡድን ላይ በሠራው ጥፋት ለአሜሪካው አጥቂ ፎላሪን ባልገን የተሰጠው ቀይ ካርድ እንዲታገድ መደረጉን ተከትሎ በፊፋ ፕሬዚዳንት ላይ ከፍተኛ ትችት ቀርቧል።
የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) አጥቂው በቀጣዩ የአገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ እንዳይሳተፍ የሚያግደው ውሳኔን የሻረው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ከገቡ በኋላ ነው።
በዓለም ዋንጫ ታሪክ 189 ጊዜ ቀይ ካርድ የተሰጠ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ቀጣዩን ጨዋታ ያለመሳተፍ ዕገዳ ተፈጻሚ ያልሆነው የአሁኑን ጨምሮ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ብቻ ነው።
የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ በሜክሲኮ እና በካናዳ አስተናጋጅነት የተካሄደ ነው።
ቅዳሜ ዕለት እንግሊዝ ከፈረንሳይ ለሦስተኝ ደረጃ የምትጫወት ሲሆን አርጀንቲና እና ስፔን ደግሞ እሁድ ዕለት ይጋጠማሉ።
