“ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ያስፈለገኝ በዘርፉ መሥራት የሚችል ዕውቀት ያለው ትውልድ ለማፍራት ነው”

Date:


ልጅ ኤልያስጥላሁን
(የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ መሥራች)


በኢትዮጵያ ‹‹ዘመናዊ›› የሚባለው የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ መኾን በጀመረበት ያለፈው አንድ ምዕተ ዓመት፣ በስፋት ከሚነሱበት ትችቶች አንዱ የትምህርት ቋንቋን የሚመለከት ነው፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማሪያ ቋንቋው ባዕድ መኾን ደግሞ ለትችቱ ቀዳሚ ምክንያት ነው፡፡

በፈጠራና ሳይንስ ዕውቀቶች የላቀ ዐቅም ያለው የተማረ ትውልድ መፍጠር ባለመቻሉ ውስጥም፣ ጽንሠ ሐሳቡ በባዕድ ቋንቋ ርቆ መቀመጡ በመግፍኤነት ይነሣል፡፡ አሁን ግን እንዲህ ላለው ተንከባላይ የትምህርት ሥርዓት ችግር ‹‹ፍቱን›› መንገድ የተቀየሰለት ይመሥላል፡፡

የዛሬው እንግዳችን ልጅ ኤልያስ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ›› ለመክፈት እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ሰው ናቸው፡፡ ለመኾኑ እንዲህ ያለው መሻታቸው ከየት ተወለደ? ትልሞቻቸውና ግቦቻቸውን ወደ ተግባር ለመተርጎምስ ምን ዐይነት ምዕራፎችን አለፉ? የእንቅስቃሴያቸው አሁናዊ ቁመናስ ምን ይመሥላል? በሚሉት ጥያቄዎች ዙርያ የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ ከግዮን ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኀተመወርቅ ጋር አድርገዋል፡፡ እንኾ!


ግዮን፡- ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?


ልጅ ኤልያስ፡- ልጅ ኤልያስ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ እስከ ሀይስኩል ያለውን ትምህርቴን የተማርኩት መርካቶ ነው፡፡ ኳስ ሜዳ አካባቢ አባቴ የእንጨት መሰንጠቂያ ነበረው፡፡ ወደ ዐሥር የሚኾኑ የመሰንጠቂያ ማሽኖች ነበሩት፡፡ እኔም በዚያ ጩኽት ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ ዘጠነኛና ዐሥረኛ ክፍል አቃቂ አድቬንቲስት አዳሪ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት፡፡ በኋላ መኖሪያችንን ወደ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አዛውረን ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ ገባን፡፡

አሜሪካን ሀገር እስክመጣ የኖርኩት እዚያው ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ ነው፡፡ አካባቢው በዲፕሎማት ሰፈርነት የሚታወቅ ነው፡፡ የነጋዴ ልጅ በመኾኔ ትምህርት ላይ ብዙም ነበርኩ፡፡ ኾኖም ግን ጥሩ ውጤት አመጣ ነበር፡፡ ለምሳሌ ማትሪክ ስፈተን ‹‹ስትሬት ቢ›› ነው ያገኘሁት፡፡ አሜሪካን ሀገር ወንድም ነበረኝ፡፡ በመጨረሻ እሱ ቪዛ ላከልኝና ወደ አሜሪካን አቀናሁ፡፡


ግዮን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሌጅ ገብተው ተምረው ነበር? ከገቡስ የትምህርት ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?


ልጅ ኤልያስ፡- በዚያን ጊዜ 3 ነጥብ ስለነበረኝ ተግባረ ዕድ ገብቼ ማርኬቲንግ መማር ጀመሬ ነበር፡፡ ኾኖም ቤተሰቦቼ ነጋዴዎች ስለነበሩ በመማር ጊዜዬን እንዳላጠፋ መከሩኝ፡፡ ታላቅ ወንድሜም ስኬታማ ነጋዴ ስለነበር እሱን ማገዝ ጀመርኩ፡፡ ያም ኾኖ ግን በማታው ፕሮግራም ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚባል ትምህርት ጀምሬ ነበር፡፡

ትምህርቱም ከሳይንስነቱና ተግባራዊ እውቀትነቱ ይልቅ መንግሥት መር በመኾኑ ብዙም አልሳበኝም ነበር፡፡ ሁለት ዓመት ተመሬ አቋረጥኩት፡፡


ግዮን፡- እስቲ ቤተሰብዎን ያስተዋውቁን?


ልጅ ኤልያስ፡- ብዙ እህቶችና ወንድሞች አሉኝ፡፡ አባቴ ሦስት ሚስቶች ነበሩት፡፡ እኔን ጨምሮ ከእናቴ የተወለዱ ስምንት ልጆች ነበሩት፡፡ አሁን ላይ ከስምንታችን አንድ ወንድማችን አርፎ ሦስት ሴትና አራት ወንዶች ቀርተናል፡፡ እኔ አራተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ከሌሎች የአባታችን ልጆች ጋር ብዙ አንቀራረብም፡፡


ግዮን፡- ከሀገር የወጡበት አጋጣሚ ምን ነበር?


ልጅ ኤልያስ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ወንድሜና ውጪ የሚኖሩ ቤተሰቦቼ ቪዛ ልከውልኝ ነው የመጣሁት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እያለሁ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር እሠራ ነበር፡፡ የሕንፃ መሣሪያ ሱቆችም ነበሩን፡፡ የሕንፃ መሣሪያ ዕቃዎች ደግሞ አብዛኞቹ ከውጭ የመጡ ናቸው፡፡ አንድ ወቅት ግን ከገበያ ላይ ጀሶ ጠፋ፡፡

ስለዚህ ጀሶ እንዴት ይሠራል? የሚለውን ነገር ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ኬሚስትሪ በግሌ አጥንቼ ብዙ ነገሮችን ማወቅ ቻልሁ፡፡ ከዚያም ናሙና ማስፈተሽ ጀመርኩ፡፡ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሄጄ ሳሳያቸው ደረጃውን አውጥተው ፈቃድ ለመስጠት ከባድ ኾነባቸው፡፡


እኔም በጊዜው የማዕድን ሕጉ ምን እንደኾነ ለማጥናት ሞከርኩ፡፡ ሳጠና ያገኘሁት ነገር የውጭ ኩባንያዎች መጥተው እንዲሠሩት እንጅ ኢትዮጵያውያን ገብተው እንዲሠሩት የሚያስችል ሁኔታ የሌለው መኾኑን ተረዳሁ፡፡ እኔ ግን ሳላቋርጥ ምርምሬን በመቀጠል በላቦራቶሪ ሳስመረምር እንደአልሙኒየም ዓይነት ከፍተኛ ንጥረ ነገር የሚወጣቸው የአፈር ዓይነቶችን አገኘሁ፡፡

ሳሳያቸውም ለዚህ ዓይነት ሥራ አጋዥ የሚኾን ሕግና ሥርዓት የለንም አሉኝ፡፡ እኔም ከሀገር እስክወጣ ድረስ በዚህ ዙሪያ በጣም እሠራ ነበር፡፡ ዓላማም ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነበር፡፡

ነገር ግን ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ያለኝ ግንኙነት ለውጥ አልባና መመላለስ ብቻ ኾነ፡፡ እኔ ራሴ አሁን ላይ ይህን የሳይንስ በአማርኛ ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ያስፈለገኝ በዘርፉ መሥራት የሚችል ዕውቀት ያለው ትውልድ ለማፍራት ነው፡፡ ምህንድስናን በደንብ የሚያውቁ ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ በራሳቸው ሀገር ቢሠሩ ሀገራችንም ትቀየራለች የሚል ጽ ዕምነት አለኝ፡፡


ግዮን፡- ከማዕድን ሚኒስቴር ፓተንት ጠይቀው እንዳልተሰጥዎት ሰምተናል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?


ልጅ ኤልያስ፡- አዎ ትክክል ነው፡፡ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጡኝ ጠይቄ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደማይሰጡኝ በደብዳቤ አሳውቀውኛል፡፡ በጊዜው ብዙ ነገሮችን አውጥቼ ነበር፡፡ አልሙኒየም ሀይድሮጅን የተባለው አፈር በኢኮኖሚ ደረጃ ሊለማ የሚችል አፈር ነው፡፡

እኔ ለማዕድን ሚኒስቴር ለዚህ ምርምር የሚጠቅም ግብዓት በጥሬው ሰጥቼ ነበር፡፡ በዚያ መሠረት ፓተንት ይሰጠኝ ስላቸው እንደማይሰጡኝ አሳወቁኝ፡፡ እኔ ደግሞ እውቅናውን የፈለግሁት ከሌሎች ተቋማት ጋር ለመሥራት እንዲረዳኝ ብዬ ነበር፡፡

እኔ በዘርፉ ትምህርት የለኝም፤ ነገር ግን በግል ጥረቴ ብረት ያለው አፈር፣ አልሙኒየም ያለው አፈር፣ በርካታ የማዕድን ዓይነቶች ያለው አፈር መለየት ችዬ ስለነበር ነው ለማዕድን ሚኒስቴር አቅርቤ ያስመረመርኩት፡፡ አሁን ላይ ሳስበው ግን፣ ይህን ሥራ ለመሥራት ከኬሚስትሪም ባለፈ ብዙ ዓይነት ዕውቀቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ በዘርፉ ደንበኛ የኮሌጅ ትምህርት ያስፈልጋል፡፡


ግዮን፡- ‹‹ልጅ ኤልያስ›› የተባሉበት ምክንያት ምንድነው?


ልጅ ኤልያስ፡- ይህን ሹመት ለራሴ የሰጠኹት ራሴው ነኝ፡፡ ለእኔ ‹‹ልጅ›› የሚለው ቃል ‹‹አቶ›› እንደሚለው ቅጽል የክብር ስም ነው፡፡ ‹‹ልጅ›› የሚል ስም ያላቸው ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ጓደኞችም አሉኝ፡፡ ይህ ስም ቤተሰብ የሚያወጣው ነው፡፡ ብዙ ሰው እኔን ከንጉሣዊ ቤተሰብ ጋር ሊያገናኘኝ ይሞክራል፡፡ በርግጥ እኔም የኢትዮጵያ ነገሥታት የሠሩትን ሥራ አብዝቼ የማከብር ሰው ነኝ፡፡ ስለዚህ ከዚያ ጋር በተያያዘ ስሙ እንደ ተጨማሪ የክብር ስም እቆጥረዋለሁ፡፡


ግዮን፡- ለምንድነው የዩኒቨርሲቲያችሁ መጠሪያ ስም ‹‹ልጅ ኤልያስ›› የኾነው?

ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን ከልጅ ኤልያስ ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ ቀጣዩን ክፍል በሚቀጥለው ይዘን የምንቀርብ ይኾናል፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 225 ግንቦት 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተገለጠ

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና አቅርቦት ላይ ተፈጥሮ የነበረው ስጋት...

አሜሪካ የኢራንን የጭነት መርከብን መያዟን አስታወቀች

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የዘጋችው...

“ቴዲ አፍሮ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ቀይሮታል!” — ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

በ"ወቸው ጉድ" ፖድካስት ላይ እንግዳ ሆነው የቀረቡት ፕሮፌሰር ብርሃኑ...