በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ የሆነውን የዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያ በማስተዋወቅ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን አንድ እርምጃ ያራመደው ዳሸን ባንክ ለ15ኛ ጊዜ የ“ዘ ባንከር” ሽልማትን ተቀዳጀ፡፡
ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ባንኮችን በተለያዩ የአፈጻጸም መለኪያዎች በመመዘን ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚሰጠውና በእንግሊዙ ፋይናንሻል ታይምስ የሚታተመው ዘ ባንከር መጽሔት፣ ዳሸን ባንክ ሁሉን በአንድ የሆነ መተግበሪያ በማስተዋወቁና ለአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ያመጣውን አበርክቶ እንደ ቁልፍ መስፈርት በመውሰድ ለ15ተኛ ጊዜ የ2025 የኢትዮጵያ የዓመቱ ምርጥ ባንክ በሚል ሰይሞታል፡፡
ሽልማቱን በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ተገኝተው የተቀበሉት የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ባደረጉት ንግግር “ዳሸን ባንክ የአመቱ የኢትዮጵያ ምርጥ ባንክ ተብሎ መሸለሙ ባንኩ የኢንዱስትሪውን ቀጣይ ጉዞ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ለመቅረጽ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።” ብለዋል፡፡
“በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፈር ቀዳጅ እንደመሆናችን መጠን የሀገሪቱን የመጀመሪያ የባንክ ሱፐር አፕ እና የዙሪያ የቢዝነስ አውቶሜሽን ማሽንን አስተዋውቀናል።” ያሉት አቶ አስፋው፣ “ወደፊትም፣ ሁሉን አካታች፣ ቀልጣፋ እና በዲጂታል መንገድ የተገነባ የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር ቁርጠኛ ነን» ሲሉ አክለዋል።
የዳሸን ሱፐር አፕ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ደንበኞችን ያፈራ፣ የባንክ እና የዕለት ተዕለት የአኗኗር አገልግሎቶችን በአንድ ደህንነቱ በተጠበቀ እና ምቹ መድረክ ላይ ያመጣ መተግበሪያ ከመሆኑም በላይ ደንበኞች በማንኛውም ጊዜ ፣ በየትኛውም ቦታ ፣ ያለማቋረጥ በ24/7 የጊዜ ዑደት ሂሳባቸውን እንዲከፍቱ ፣ እንዲያስተዳድሩ እና እንዲገለገሉ አስችሏል።
ዳሸን ሱፐር አፕ በአንድ መተግበሪያ ሙሉ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ፣ተለዋዋጭ የኪው አር (QR) ክፍያዎች የሚፈፀሙበት፣ የበጀት አስተዳደር ያለው፣የነዳጅና የትምህርት ቤት ክፍያ ክፍያዎች በቀላሉ የሚከናወንበት፣ ቻት ባንኪንግን የተላበሰ፣ህይወትን የሚያቀሉ ትናንሽ የግብይት መተግበሪያዎች (ሚኒ አፖች) በውስጡ የያዘ ለሁሉም ስልኮች የሚሆን የዩኤስኤስዲ አማራጭ ይዞ የቀረበ ነው፡፡በተጨማሪም በቅርቡ የዲጂታል ብድርና ቁጠባ፣የካርድ አስተዳደርና ሌሎች አገልግሎቶችን ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
