የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ “ድል ወደ መቀዳጀት እያመራን ነው” በማለት የጀመሩት ወታደራዊ እርምጃ እንደሚቀጥል ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራቸው የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ውስጥ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ዛሬ የተነገረውንና እስራኤል የኢራን ዋና ከተማ – ቴህራንን የአየር ክልል በቁጥጥሯ ሥር ማስገባቷን” ደግመው ተናግረዋል።
በዚህ ጦርነት “ግባችን የሆኑትን ሁለት ጉዳዮች ለማሳካት እየሠራን ነው፤ እነሱም የኒውክሌር ስጋቶችን ማስወገድ እና የሚሳዔል ስጋቶችን ማጥፋት ናቸው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኔታኒያሁ አሁን አገራቱ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ጥቃቶች በሁለት የለዩ ሲሆን፣ የእስራኤል ዒላማዎች የኒውክሌር እና የሚሳዔል ማዕከላት ናቸው ሲሉ፤ የኢራንን ደግሞ “ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው” ብለዋል።
“ለቴህራን ነዋሪዎች ዒላማ የሚሆኑ ቦታዎችን ‘ለቃችሁ ውጡ’ እንላለን፤ ከዚያም እርምጃ እንወስዳለን” በማለት የአገራቸው ሠራዊት የሚወስደውን እርምጃ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአየር ኃይሉ ሠፈር ውስጥ ለሚሰሩት ዜጎቻቸው ምስጋና አቅርበው “በእግዚአብሔር ድጋፍ እርምጃ እየወሰድን ድል እስክንቀዳጅ ድረስ እንቀጥላለን።” ብለዋል።
እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈተችበት ካለፈው አርብ ጀምሮ ቢያንስ 224 ሰዎች መገደላቸውን የኢራን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
