በመጀመሪያ ሀላፊነታቸው ከፌዴሬሽኑ የተሰጣቸው ግብ በሴካፋ በቻን እና በአፍሪካ ዋንጫ ማብቃት እንደነበር ያስታወሱት አሰልጣኙ ዋልያዎቹን ለሴካፉ እና ለቻን ውድድር ላይ ቢያበቁም ለአፍሪካ ዋንጫ አለማሳለፋቸው እንደሚያስቆጫቸው ተናግረዋል።
“ከ10 ዓመት በፊት ከሀላፊነቴ የተነሳሁት በውጤት ማጣት ሳይሆን በሌሎች ምከንያቶች ነው” ያሉት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በወቅቱ ዕድል የሰጧቸው ወጣቶች እንደ ጋቶች ፓኖም፣አስቻለው ታመነ እና ሌሎችም በኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስ ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አንስተዋል።
ከኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ እና አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ ብዙ ተምሬያለሁ ያሉት አሰልጣኙ ወደ እዚህ ቦታ የመጣሁት ሀገሬን ለማገልገል እንጂ የግለሰቦችን ሀሳብ ለማራመድ እና ጉቦኛ ለመሆን አልመጣሁም ሲሉ ገልፀዋል።
አሰልጣኙ ኢትዮጵያዊ ከመሆኔ ባለፈ የወታደር ልጅ መሆኔ ሀገርን ማገልገል ምን ማለት እንደሆነ አውቀዋለው ብለዋል፡፡
የስልጠና መንገዴን ምተገብረው በተጫዋቾቼ አቅም ነው ያሉት አሰልጣኙ በሊጉ ያሉ እና ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን እንደሚመርጡም ተናግረዋል። የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ላይ የታየውን ተስፋም ለማስቀጥል መዘጋጀታቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡
