ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 40 የሚደርሱ የአሠራር መመሪያዎችና ፖሊሲዎችን አዘጋጀ

Date:


ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ለሚያደርገው ጉዞ በበርካታ ዝግጅቶች እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ ለዚህም መሳካት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች የውጭ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘንድ ልምድ በመውሰድ 40 የሚደርሱ የአሠራር መመሪያዎችና ፖሊሲዎችን ማዘጋጀቱን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን አስታውቀዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ “ከፍተኛ ትምህርት ለላቀ ተፅዕኖ” በሚል መሪ ቃል ከትናንት ሐምሌ 28 ቀን 2017 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚህም ጉባኤ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሽኔ እና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ ሮ ደብሬ የኋላን ጨምሮ፤ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ቴክኖሎጅ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።

በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ/ር) “የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የአጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ100ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት መካሄዱ ልዩ ድምቀት ሆኗል” ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ በተማሪዎችና በማኀበረሰቡ መካከል ጥብቅ ቁርኝት እየፈጠረ የሚገኘው የጎንደር የቃል ኪዳን ቤተሰብ ለውጥ ማምጣቱን የገለጹም ሲሆን፤ በሰላም ሚኒስቴር ጅምሩ ተቀባይነት አግኝቶ በቅርቡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሚኒስቴሩ መካከል የመግባቢያ ስምምነት መፈጸሙን አስታውሰዋል።

ዩንቨርስቲው በአሁኑ ወቅት 365 መርሃ ግብሮች እና 11 ሺሕ 150 ሠራተኞች እንዳሉት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በተጨማሪም 22 ግቢዎችና 11 ኮሌጆች እንዳሉት ተናግረዋል።

በማስተማር፣ ምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ዩኒቨርስቲው ያበረከታቸው ክንውኖች፤ የትምህርት ሚኒስቴር የለውጥ አቅጣጫዎች ያስከተላቸው አዎንታዊ ውጤቶች መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ በበርካታ ዝግጅቶች እያከናወነ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም መሳካት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች የውጭ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘንድ ልምድ በመውሰድ 40 የሚደርሱ የአሠራር መመሪያዎችና ፖሊሲዎችን መዘጋጀታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በቁልፍ ውጤት አመላካች እንዲሁም የ”አክሪዲቴሽን” ሥራዎች ዘርፍም ስኬታማ ውጤቶችን ማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም በኢትዮጵያ ጥራትና ትምህርት ሥልጠና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ “አክርዲቲሺን” በ”አንስቴዢያ” ሥልጠና ዘርፍ ማሳካቱን በመግለጽ፤ በሌሎች ዘርፎችም የተጠናከረ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ ለማድረግ የሚካሄደው ለውጥ የሚደነቅ መመሆኑን በማንሳትም፤ “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአዲስ አሠራር እና የለውጥ ሐዋርያ ናቸው” ብለዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ም/ ከንቲባና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ደብሬ የኃላ፤ ጎንደር በኢትዮጵያ ስርዓተ መንግሥት ግንባታ ላይ የራሷን አስተዋፅዖ መወጣቷን ተናግረዋል፡፡

አክለውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሕብረተሰብ ጤና ማሰልጠኛ ተቋም ምስረታ ጋር ተያይዞ በዘመናዊ የትምህርት ታሪክ ሂደት ላይ የራሱን አስተዋዖ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ችግር ለመቅረፍ የትምህርት ፖሊሲ፣ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያዎች፣ ምቹ የትምህርት ቤት ግንባታዎችና ማሰልጠኛዎችን እየተሰሩ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ ሰፊ ሥራ የሚቀረው ዘርፍ ስለመሆኑን ጠቁመዋል።

“ጎንደር ከተማ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአንድ ሳንቲም ገፅታዎች ናቸው” ያሉት ወ/ሮ ደብሬ፤ “ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ትልቅ ጉባኤ ጎንደር ከተማ ላይ በማካሄዱ ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል” ብለዋል።

በጉኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮሪ ጡሹኔ በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ለማሳደግ ጥረቶች ቢኖሩም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በርካታ ሥራዎች ይጠበቃሉ” ብለዋል።

ጉባኤው በየዓመቱ የሚካሄድ ስለመሆኑ በመግለጽም፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ሂደት ለመገምገም እና የቀጣይ ዓመት ዕቅድን ለመቀየስ ያለመ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በመግለጽ፤ ከእነዚህም መካከል የመምህራን ልማት፣ ግብዓት ማሟላት፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት መከታተል እና ውጤቱን መለካት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ ለመሆን እያደረጉት ያለው ዝግጅት እና የብቃት ማረጋገጫ ዝግጅት በጉባኤው እንደሚገመገም ተናግረዋል፡፡

“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቆጣቢና ውጤታማ በሆነ መንገድ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት እና በቴክኖሎጅ በመታገዝ የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነትን፣ አካታችነትንና ጥራትን ለማሳደግ ጠንክረው መስራት አለባቸው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ በዛሬው ዕለትም መካሄዱን ቀጥሎ የተለያዩ ውይይቶች እና ጉብኝቶች በዩኒቨርስቲው በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

(አሐዱ ሬዲዮ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ በቋሚነት መኖር የሚያስችላቸው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ከበኦሞ...

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...