ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይን በብሔራዊ ቤተመንግሥት ተቀብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገለፃ፣ ጉብኝቱ የወል ፍላጎት በሆኑ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶችን እንደሚያካትት ይጠበቃል።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉት ጉብኝት ከታህሳስ 29 እስከ ጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም በአፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉት ጉብኝት አካል መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ይህም ጉብኝት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሶቶን እንደሚያካትትም ተመላክቷል።
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት በሚካሄደው የቻይና-አፍሪካ “የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት” የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ጉብኝት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዓመቱ መጀመሪያ የውጭ አገር ጉብኝታቸውን ወደ አፍሪካ በማድረግ ለ36 ተከታታይ ዓመታት የዘለቀውን ልማድ ያስቀጠለ ሲሆን፣ ይህም ቤጂንግ ለአህጉሪቱ የምትሰጠውን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ትኩረት በግልጽ ያሳያል ተብሏል።
