እስራኤል በኢራን ላይ የምታካሂደው ዘመቻ ሲጠናቀቅ ለኅልውናዋ ስጋት የሚሆን የጦር መሳሪያ በኢራን እጅ ላይ አይኖርም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከኢራን በኩል ያሉ የኒውክሌር ስጋቶችን “ታስወግዳለች” ብለዋል ዛሬ ማለዳ ላይ በኢራን ሚሳዔል የተመታውን ሶሮካ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት።
“ይህ ተልዕኮ ሲያበቃ ለእስራኤል ስጋት የሚሆኑ የኒውክሌር ስጋቶች እንዲሁም የባለስቲክ ሚሳዔል ስጋቶች በሙሉ አይኖሩም” በማለት ኔታኒያሁ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ኔታኒያሁ ጨምረውም እስራኤል በኢራን ላይ ባለፉት ሰባት ቀናት በፈፀመቻቸው ጥቃቶች የኒውክሌር ፕሮግራሟ “እጅጉን” እንደተጎዳ አመልክተዋል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በእስራኤል ጥቃት ዒላማ ሊደረጉ እንደሚችሉ ተጠይቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም “ማንም ከዒላማችን ውጪ አይሆንም” ብለዋል።
ከአሜሪካ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው እና ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ያላቸው ወዳጅነትም “ድንቅ” መሆኑን የገለጹት ኔታኒያሁ፤ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር “ከሞላ ጎደል በየዕለቱ” እንደሚወያዩ ተናግረዋል።
BBC Amharic
