የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ፣ በአየር መንገዱ ውስጥ የታዩ የ”አመራር እና የአስተዳደር ድክመቶችን” ለመቅረፍ የቀድሞውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄን የኡጋንዳ አየር መንገድ ጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ አማካሪ እና ባለሙያ አድርገው መሾሙን የኡጋንዳ መንግሥት በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፉት በብሔራዊ አየር መንገዱ ውስጥ የሚታዩ በርካታ የአስተዳደር እና የአመራር ድክመቶችን ለማስተካከል ሲሆን እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም ድረስ አዲስ ቋሚ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስኪቀጠር ድረስ አቶ ግርማ ዋቄ ተቋሙን በኃላፊነት እንዲመሩ ተመድበዋል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ አየር መንገዱን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት ጄኒፈር ባሙቱራኪ ወዲያውኑ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱና ቦታውን እንዲያስረክቡ የታዘዘ ሲሆን እርሳቸውም ከአጋማሽ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በጊዜያዊነት በኋላም በቋሚነት ሲያገለግሉ ቆይተው አሁን ከሥራቸው ተሰናብተዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚና እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ያገለገሉት አቶ ግርማ ዋቄ አየር መንገዱን ወደ ተሻለ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያሸጋግሩት ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
አቶ ግርማ ዋቄ አየር መንገዱን እስከ ሐምሌ 2026 (July 2026) ድረስ በጊዜያዊነት የሚመሩ ሲሆን፣ በዚህ ቆይታቸው አዲስ ቋሚ የአመራር ቡድን እንዲዋቀር እና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ይሰራል ተብሏል።
ግርማ ዋቄ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአፍሪካ ግዙፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስቻሉ አንጋፋ መሪ በመሆናቸው፣ ይህ ሹመት ኡጋንዳ ለአየር መንገዷ እድገት የወሰደችው ቁርጠኛ እርምጃ እንደሆነ ታይቷል።
“ይህ ሹመት ለይስሙላ የተደረገ የአማካሪነት ሚና ሳይሆን፣ አየር መንገዱን ከገባበት የአሰራር ዝቅጠት ለማውጣት የተሰጠ ቀጥተኛ የአስፈጻሚነት ስልጣን ነው” ሲል የሶፍት ፓወር (SoftPower) ዘገባ አመልክቷል።
ይህ ዜና በአፍሪካ አቪዬሽን ላይ ያለውን የኢትዮጵያውያንን ተጽዕኖ ዳግም ያሳየ ክስተት ነው።
ኢትዮ ኤፍ ኤም
