- ያረገዝሽው ልጅ ጾታ ከውጪ ታይቶ ይታወቃል::
ሆድሽ ወይ ወገብሽ እንዲህ እና እንዲያ ስለሆነ፣ እርግዝናው “ስለቀለለሽ” ወይም “ስለከበደሽ” የልጅሽ ጾታ ሴት ወይም ወንድ ነው ብሎ መተንበይ አይቻልም። የልጅሽን ጾታ ማወቅ የምትችዪው አምስተኛ ወር ከገባሽ በኋላ በአልትራሳውንድ ምርመራ ነው።
- እርጉዝ ሆነሽ ለውዝ እና ወተት ከወሰድሽ ልጅሽ ላይ አለርጂ ያመጣል::
አንቺ ራስሽ የለውዝ እና የወተት አለርጂ ከሌለብሽ በቀር፣ አንቺ የምትበዪው የትኛውም ምግብ ልጅሽ ላይ አለርጂ ሊያመጣ አይችልም።
- ማቅለሽለሽ ጠዋት ጠዋት ብቻ የሚያጋጥም ነው::
ማቅለሽለሽ ብዙ ጊዜ ጠዋት ጠዋት ቢጀምርም በቀን በየትኛውም ሰዓት ሊያጋጥም ይችላል። “morning sickness” የሚለው የእንግሊዝኛ መጠሪያው እንደሚለው ጠዋት ጠዋት ብቻ አይመጣም።
- እርጉዝ ከሆንሽ ስፖርት መሥራት የለብሽም::
በእርግዝና ጊዜ ተገቢ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ በእጅጉ የሚመከር ነው። የእለት ተእለት ተግባርሽን ከማከናወን በተጨማሪ ለነፍሰ ጡር የሚስማሙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ብታደርጊ፣ ለወሊድ በተሻለ ዝግጁ ያደርግሻል። (ስለ እርግዝና ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ/ስፖርት የበለጠ የምንለው ይኖራል)
- በእርግዝና ጊዜ ጾታዊ ግንኙነት ማድረግ ልጁ ላይ ጉዳት ያመጣል::
በተለየ የጤና ችግር ምክንያት ሐኪም ካልከለከለሽ በቀር በእርግዝና ጊዜ ጾታዊ ግንኙነት ማድረግ (ወሲብ መፈጸም) ምንም ችግር አያመጣም፤ ምጥ አያመጣም፤ ጽንስ እንዲቋረጥም አያደርግም።
- የምትበዪው ምግብ “ለሁለት ሰው” መሆን አለበት::
እርጉዝ ስትሆኚ የምትበዪው ምግብ መጠን መጨመር አለበት፤ ክብደትሽም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይጨምራል። ይሁን እንጂ “ሁለት ነፍስ ነኝ” በሚል ያን ያህል ከፍተኛ ለውጥ ሊኖረው አይገባም። በአማካይ እርጉዝ ሴት ሌላ ጊዜ ከምትበላው ምግብ 10 በመቶ ተጨማሪ ምግብ መመገብ ይኖርባታል።
- ትንሽ አልኮል መቀማመስ ችግር የለውም::
በእርግዝና በየትኛውም ደረጃ አልኮል ያላቸው ማናቸውንም መጠጦች (ቤት የሚዘጋጁ እንደ ጠላ እና ጠጅ ያሉትን ጨምሮ) ማስወገድ ያስፈልጋል። አልኮል የልጅሽን የአእምሮ እድገት ይጎዳል። የልጅሽ የአእምሮ ጤንነት ከየትኛውም አምሮት ይበልጣል።
- እርጉዝ ሆነሽ ጥሬ ሥጋ ካማረሽ ብትበዪ ችግር የለውም::
ጥሬ ሥጋ በእርግዝና ጊዜ ሙሉ በሙሉ ማቆም አለብሽ። ድንገት በልተሽ ፓራሳይት ቢገኝብሽ፣ ፓራሳይቱ ጽንሱ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፤ ለዚሁ የሚሆን መድኃኒት ልውሰድ ብትዪም እሱም ችግር ያመጣል።
- እርጉዝ ከሆንሽ ቡና እርግፍ አድርገሽ መተው አለብሽ::
በእርግዝና ጊዜ አንድ ወይም ሁለት ስኒ ቡና መጠጣት ችግር እንደሌለው ጥናቶች አረጋግጠዋል።
- እርጉዝ ስትሆኚ የግድ ያልተለመደ ነገር ያምርሻል::
ብዙ እርጉዝ ሴቶች ልዩ ልዩ “አምሮት” ቢሰማቸውም፣ ሌሎች ብዙ እርጉዝ ሴቶች ደግሞ ምንም ነገር ላያምራቸው ይችላል። እርጉዝ ስለሆንሽ የግድ የሚያምርሽ ነገር ይኖራል ማለት አይደለም። የአምሮት ስሜት በሰውነት ውስጥ ከሚገኙ ሆርሞኖች መለዋወጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል ነው።
