በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፤
“… መጠለያን፥ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ ስደተኛውን ይወድዳል።”
(ዘዳግም ፲፤፲፰)፤
“… ስደተኛውን አትበድለው፥ ግፍም አታድርግበት።”
(ዘጸአት ፳፪፤፳፩)፤
” እንግዳ [ስደተኛ] ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፤”
(ማቴዎስ ፳፭:፴፭)፤
“… በዛች ምድር ለእውነት፣ ለፍትሕ የቆመ ሐቀኛ፣ ቅን የሆነ የሐበሻ ንጉሥ፤ ስደተኞችን በፍቅር ተቀብሎ የሚያስተናግድ፤ እንግዳ አክባሪ ደግ ሕዝብን ታገኛላችሁ፤ ወዳጆቼ እባካችሁ ነፍሳችሁን አድኑ ከክፉዎች፣ ከዓመፀኞች ቁጣና ሰይፍ ራሳችሁን አድኑ፣ የሰላም ጌታ፣ የአላህ እዝነት ከእናንተ ጋር ይሁን…!!”
~ ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.)
ትንሹ “ሂጂራ” ወደ አክሱም/ኢትዮጵያ፡-
የዛሬው ጽሑፌን ፈር ለማስያዝ በአንድ ገጠመኜ መነሻነት ልንደረደር ወደድኹ፤ ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ በኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርግ አንድ አሜሪካዊ ወጣት ጋር ተገናኝተን ነበር፡፡
ይህ ወጣት አሜሪካዊ የሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን ወደሀገራችን የመጣበት ምክንያት ደግሞ፤ ለድኅረ ምረቃ/ለሁለተኛ ድግሪ ትምህርቱ መመረቂያ ማሟያ የሚሆነውን የጥናት ድርሳኑን፤ ‹‹The Little Hìjìra to Aksum›› በሚል አርእስት ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችለውን የታሪክ፤ የጹሑፍና የቃል/ትውፊታዊ መረጃዎችን ለመስብሰብ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ወርኻ ክረምት ላይ ከዚህ አሜሪካዊ ወጣት ጋር ለዚሁ ጥናት ሥራው የሚያስፈልገውን መረጃዎች የማሰባሰብ ሂደት ለማገዝና ለማስተርጎም ሥራ ወደ ታሪካዊቷ ትግራይ ክልል አብረን ተጉዘን ነበር፡፡ የዚህ የመስክ ጉዞ ሥራ ዋና ዓላማውም፤ የመጀመሪያዎቹ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች/ሱሃባዎች ከሳውዲ ዐረቢያ ወደኢትዮጵያ/አክሱም ግዛት ያደረጉትን “ሂጅራ” በተመለከተ መረጃዎችን ለመስብሰብ ነበር፡፡
የዚህ ጥናት የመስክ ጉዞ አንዱና ዋንኛ መዳረሻችን የነበረው ደግሞ በኢስላም አባቶችና ምሁራን ዘንድ- “የእስልምና ሃይማኖትን በሰላም ተቀብሎና በምድሩ ላይም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በነጻነትና በሰላም እንዲኖሩ ፈቅዷል፤” ተብሎ በሚታመነው በኢትዮጵያዊው ንጉሥ አርማሕ (አልነጃሺ) ስም የታነፀው መስጊድ ነበር፡፡
በአልነጃሺ መስጊድ ጉብኝት ቆይታችንም ያገኘናቸው የሃይማኖቱ ታላላቅ አባቶችና ሼኽዎች ወደዚህ ቅዱስ ስፍራ የመጣንበትን ጉዳይ በትሕትና አስረዳናቸው፡፡
የአልነጃሺ መስጊድ ሼኽዎችና የእምነቱ ታላላቅ አባቶች በኢትዮጵያዊ መልካም መስተንግዶ፤ በፍቅርና በሰላም ተቀብለውን በክብር አስተናገዱን፡፡
በአልነጃሺ መስጊድ ቆይታችንም እነዚህ የሃይማኖቱ መምህራን ኢስላም በተወለደበት በሳውዲ ዐረቢያ ምድር (መካ እና መዲና) ገና በሁለት እግሩ ከመቆሙ በፊት በኢትዮጵያ ምድር በሰላም ተዘርቶ ያበበትን የኢስላምን ወርቃማ የታሪክ ዘመንን፤ በታሪክ ሰነዶችና በትውፊት/በቃል ከሃይማኖቱ ታላላቅ አባቶች ዘንድ የተላለፈላቸውን መሳጭ ታሪክ በሰፊው ተረኩልን፡፡
እንደ ኢስላም ሃይማኖት አስተምህሮም፤
ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) በዘመናቸው በሕዝባቸው መካከል የነገሠውን የሞራል ውድቀት፣ የሥነ-ምግባር ዝቅጠትና የባዕድ አምልኮ መንሰራፋት ለማጥፋት በአላህ የተመረጡ ታላቅ ነቢይ ነበሩ፡፡
ታዲያ ነቢዩ መሐመድ ሕዝባቸውን፤ “ከባዕድ አምልኮ ራቁ፣ አላህን ብቻ እመኑ፣ እርሱን ብቻ ተከተሉ፣ ፍሩ፣ ክፋትንና ጥላቻን ተጸየፉ፣ ከእኩይ ሥራ ራቁ፣ ለፍትሕና ለእውነት ቁሙ…!!” የሚለው የኢስላም ሃይማኖት አስተምህሮአቸው በዘመኑ ከነበሩ ከሳውዲ የቋረሽ ጎሳ ሹማምንትና ባለሟሎች ዘንድ ከባድና አስጨናቂ የኾነ ተቃውሞን አስነስቶባቸው ነበር፡፡
ነቢዩ መሐመድ ግን በዚህ ከጠላቶቻቸው በተነሳባቸው ተቃውሞ፣ ስደትና መከራ በፍፁም አልተበገሩም፤ እናም ለተከታዮቻቸውም እንዲህ አሏቸው፤
“… እኔ እዚሁ ሆኜ ከአላህ፤ ከጌታዬ ለተሰጠኝ ሃይማኖት በትዕግሥት፣ በጽናት የመጣውን ሁሉ እቀበላለሁ፡፡ ለኢስላም ሞትንም ቢሆን ለመቀበል እንኳን ሳይቀር ቆርጫለሁ፤ እናንተ የአላህ ፍሬዎቼ፣ እውነተኛ ወዳጆቼ የሆናችሁ ተከታዮቼ- የክፉዎች መከራ፣ የወደረኞቻችን የጭካኔ ሰይፍ በእናንተ ነፍስ ላይ ያልፍ ዘንድ አልፈቅድም…!!
የእናንተ መከራ ለእኔ ይሁን! እናም ወገኖቼ ለነፍሳችሁ እረፍትን፣ ሰላምን፣ ፍትሕን ወደምታገኙበት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት፣ ወደ ሐበሻ ምድር በፍጥነት ሂዱ፣ ሽሹ… ፍጠኑ ነፍሳችሁን ከጨካኞች ሰይፍ አድኑ፤
በዛች በኢትዮጵያ ምድር ለእውነት፣ ለፍትሕ የቆመ ሐቀኛ፣ ደግ የሆነ የሐበሻ ንጉሥን ታገኛላችሁ… ወዳጆቼ እባካችሁ ነፍሳችሁን ከክፉዎች፣ ከዓመፀኞች ቁጣና ሰይፍ አድኑ፣ የሰላም ጌታ፣ የአላህ እዝነት ከእናንተ ጋር ይሁን!” በማለት ነቢዩ ተከታዮቻቸውን ወደ አክሱም/ኢትዮጵያ ምድር በሰላም ሸኟቸው፡፡
እንግዲህ የኢስላም ሃይማኖት ሊቃውንት አባቶች እንደሚያስተምሩት፤ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ ምድር ያደረጉት ሂጅራ/የስደት ጉዞ፤ ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) ከመካ ወደ መዲና ካደረጉት ታላቁ ሂጂራ በፊት የተደረገ “the Little Hìjìrà/ትንሹ ሂጂራ” መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በነቢዩ መሐመድ መልካም የምክር ቃል ባሕር አቋርጠው ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የመጡትን የነቢዩ ተከታዮችን/ሱሃባዎችን ጠላቶቻቸው ግን እስኪያጠፏቸው ዘንድ እረፍትን አልፈለጉም፡፡ እናም የቋረሽ ሹማምንት ወደ አክሱም ንጉሥ አርማህ ወርቅና የከበረ ስጦታን የያዙ መልእክተኞችን በፍጥነት እንዲህ ሲሉ ላኩ፤
“የተከበረክ የኢትዮጵያ ንጉሥ አርማህ ሆይ! ወደግዛትህ የመጡ እነዚህ ሰዎች ሕዝብን ያወኩ፣ እምነታችንን ያረከሱ/መናፍቃን፣ ክፉዎችና ዓመፀኞች ናቸውና እጃቸውን ይዘህ ወደእኛ ትልክልን ዘንድ እንለምንሃለን፣ እናማጽንሃለን!!”
የቋረሽ ገዥ መልእክተኞችን በቤተ-መንግሥቱ የተቀበሏቸው የአክሱም ገዥ፣ ንጉሥ አርማህ ወደ ግዛቱ የገቡ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮችን ወደ እርሱ አስጠርቶ በጠላቶቻቸው ዘንድ የተከሰሱበትን ክስና ስለሃይማኖታቸው አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አቀረቡላቸው፡፡
በአክሱም ንጉሥና በኢትዮጵያ ቤ/ክ ሊቃውንት ፊት ዘንድ የቀረቡት የነቢዩ መሐመድ ተከታዮችም የቀርበባቸው ክስ ሐሰት መሆኑንና ወደ ኢትዮጵያ ግዛት፣ ወደተከበረው የሐበሻ ንጉሥ የመጡትም፣ ፍትሕንና ሰላምን ሽተው፣ ከአሳዳጆቻቸው ዘንድ መጠጊያና መሸሸጊያ ፈልገው እንደሆነ የታላቁን ጌታ፣ የአላህን ስም ጠርተው አስረዱ፡፡
ለወጋችን ሽብልቅ ይሆን ዘንድ እዚህች ጋር ከታሪክ ማስረጃ እናጣቅስ እስቲ፤
በ 8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ የነቢዩ መሐመድን የሕይወት ታሪክን የጻፈው – ኢብን ኢሻቅ የተባለ የዐረብ ምሁር እንደሚነግረን፤ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች/ሱሃባዎች ከነበሩት መካከል ከጃፋር አቡ ጣሊብ ጋር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አስተምህሮ ላይ በነበራቸው ውይይት ወቅት በኢስላም አስተምህሮ ያለውን እውነት ሲገልጹላቸው- የሐበሻው ንጉሥ አርማህና ሊቀ ጳጳሱ ልባቸው ተነክቶ ማልቀሳቸውን ይተርክልናል፡፡
የአክሱም ንጉሥ አርማሕ ከውውይቱ በኋላ ከሳውዲ ዐረቢያ ለመጡት የቋረሽ መልእክቶኞች እንዲህ አሏቸው፤
ወደ ግዛቴ የገቡ እነዚህ ሰዎች በአስተምህሮቸው ዘንድ አንዳችም ክፉ ነገርን አላገኘንባቸውም። መጠለያ፣ መሸሸጊያ ፈልገው የተማጸኑንን እነዚህን ሰዎች፣ የምድሬን ስደተኞች አሳልፈን አንሰጣችሁም፡፡ የሃይማኖታችን መምህር የኾነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን አላስተማረንም።
እነዚህ ሰዎች ፍትሕን፣ ሰላምን ሽተው ወደ እኛ መጥተዋል፤ በግዛታችን ተጠልለዋልና በእውነት እንጠብቃቸው ዘንድ ይገባናል። እናንተም ጠላትነትን፣ ክፋትንና ጥላቻን ትታችሁ በግዛቴ በሰላም ለመኖር ከፈለጋችሁ እኔም ሕዝቤም በፍቅርና በሰላም እንቀበላችኋለን። በዚህ ለመኖር ፈቃዳችሁ ካልሆነም በሰላም ወደ ሀገራችሁ መመለስ ትችላላችሁ። በማለት አሰናበቷቸው።
በሳውዲ ዐረቢያና መካከለኛው ምሥራቅ ስደትና መከራ የገጠመው የእስልምና ሃይማኖት በኢትዮጵያ ምድር- በአክሱም ግዛት እንደ ክርስትና ሃይማኖት ሁሉ በሰላም፣ በነጻነት ተዘርቶ ለመብቀል ቻለ። ይህን አስደናቂ የሆነውን እና ለሁለቱ ታላላቅ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃይማኖቶች የሰላም ቤት ስለሆነችው ኢትዮጵያ/አክሱም በተመለከተ፤
በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር የትምህርት ክፍል- የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪና የእስልምና ሃይማኖት ምሁር የነበሩት ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ፤ “Aksum in Muslim Historical Tradition” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንዲህ ይላሉ፤
“… Aksum possesses the unique distinction of being at once the cradle of both Christianity and Islam in Ethiopia, and perhaps represents the earliest example of a geographical setting favorable for a peaceful encounter and harmonious coexistence between two great monotheistic religions: Christianity and Islam.”
ጥንታውያን ኢትዮጵውያን የእስልምና ሃይማኖት ታላላቅ አባቶች እንደሚሉት- ነቢዩ መሐመድን ተከታዮች በግዛቱ በሰላም ተቀብሎ ያስተናገደው የአክሱም ንጉሥ የነበረው ንጉሥ አርማህ ነቢዩ መሐመድን ለመጎብኘት
ወደ መካ ለመሔድ ሲዘጋጅ ሳለ ሞት እንደቀደመው
በሚከተለው ትውፊታዊ የመንዙማ ግጥም ያስታውሳሉ፤
“ወዳንቱ ሲመጣ ወዳንቱ ሲሸሽ፣
ትግሬ ላይ የቀረው ወዳጅዎ አል-ነጃሽ፡፡
ታሪክ እንደሚመሰክርልን ኢትዮጵያ ለሙስሊሙ ዓለም ታላቅ ባለውለታ የሆነች ሀገር ናት፡፡ በዛ ክፉ ዘመን ለነቢዩ መሐመድና ለተከታዮቻቸው ጥላ ከለላ የሆነች ሀገራችን ኢትዮጵያ በእስልምናው ዓለም ልዩ ስፍራ አሰጥቷታል።
ከላይ በጠቀስኩት ጥናታዊ ሥራቸው ፕሮፌሰር ሁሴን አሕመድ፤ al-Tiraz al-Manqush fi Mahasin al-Habush (The Colored Brocade on the Good Qualities of the Ethiopian) በሚል ርእስ-መሀመድ አብዱል ባኪ አል ማቅዚ እ.አ.አ. በ1583 የጻፉትን ታሪካዊ ሰነድ ዋቢ አድርገው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በነቢዩ መሐመድ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነትና ተቀባይነት፤ ክብር እንዲህ ገልጸውታል።
“who brings an Ethiopian man or woman into his house brings the blessings of God there.”
ይህ ልቦለድ ታሪክ ወይም የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ይህ በኢትዮጵያ ምድር፣ በአክሱም ግዛት ከ1400 ዓመታት ገደማ በፊት የኾነ በኢትዮጵያ ምድር የኢስላም ሃይማኖት ወርቃማ ታሪክ አንድ ዐቢይ አካል ነው።
ይሄ ዓለም ሁሉ በአድናቆት፤ በአግራሞት እጁን በአፉ ላይ እንዲጭን የተገደደበት፤ ፍቅር ያሸነፈበት፤ እውነትና የፍትሕ ድል የነሳበት፤ ከፈጣሪ ዘንድ ለሰው ልጆች ሁሉ የተቸረ የሕሊና ነጻነት፤ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃዱና የመንፈስ ልእልናው ከፍ ያለበት አኩሪ የታሪካችን አካል ነው።
በእውነት ነው የምላችሁ ለጸሎትም ሆነ ለጉብኝት በጥንታዊውና በታሪካዊው የአልነጃሽ መስጊድ፤ በነቢዩ መሐመድ የመጀመሪያዎቹ ተከታዮች/ሱሃባዎች መካነ መቃብር መካከል በርጋታ ስታልፉ የሚሰማችሁ ስሜት የከበረና ታላቅ ነው። ይኸውም ሰው የመሆን ክብር፤ ታላቅና ጥልቅ የመንፈስ ልእልና፤ ለሕሊና ነጻነት፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ከፈጣሪ ዘንድ ለተቸረ ነጻ ፈቃድ፤ ለፍትሕና ለእውነት በጽናት ዘብ የቆመ ኢትዮጵያዊ ማንነት፤ የሰው ልጅነት – እንደ ሐውልቱ ሁሉ በአክሱም ምድር ሕያው ምስክር ሆኖ ጸንቶ ቆሟል!!
እውነት ወደ ነገሠባት ፍትሕ ወደ ሚበየንባት ወደ ኢትዮጵያ ምድር፤ ወደ አክሱም ግዛት ሂዱ፤ በዛ ለእውነት በጽናት የቆመ፤ ለፍትሕ የሚሟገት የሐበሻ ንጉሥ፤ ስደተኞችን በፍቅር ዓይን የሚያይ፤ ደግና እንግዳ ተቀባይ የሆነ ሕዝብ አለና… ወደ ኢትዮጵያ፤ ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ… ሽሹ…!!
እንደ መውጫም፤ እንደ መቆዘሚያም፤
ዛሬ ከዚህ ዓለም በኩራት ከሚተርከው ታሪካችን ባሻገር አንድ ጥያቄ ራሳችንን እንጠይቅ ዘንድ ግድ ይለናል፤
ይኸውም፤ ደም እያጠለልን፤ አጥንት እየቆጠርን ሰይፍ በምንማዘዝባት፤ በጎሳና በነገድ፤ በሃይማኖት ልዩነት እርስ በርሳችን በጥላቻ በምንገፋፋበት፤ በምንገዳደልባት ኢትዮጵያ – የሕሊና ሚዛን፤ ሰው የመሆን ክብር መገለጫ፤ የፍትሕና የእውነት ተምሳሌት አድርገው ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ)፤ ዓለም ሁሉ የመሰከሩለት ኢትዮጵያዊነት ሰው የመሆን ፍቅርና ክብርና፤ ለእውነትና ለፍትሕ በጽናት የመቆም ታላቅነት ዛሬ ወዴየት አለ…?!
ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-ፈጥር በዓል አደረሳችሁ!!፤
ሰላም!!
