በሀገሪቱ እየታረሰ ከሚገኘው መሬት ውስጥ 43 በመቶ አሲዳማ አፈርን ይወክላል ተብሎ እንደሚገመት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የአፈር እና ውሃ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን ደሳለኝ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ጉዳዩን አስመልክቶ በተከናወነ ጥናት 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በአሲድ እንደተጠቃ ተረጋግጧል፡፡
ከእዚህም ውስጥ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር ለሚሆነው መሬት አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ዳይሬክተሩ “አሲዳማነቱ በጊዜው ካልታከመ በላይኛው አፈር ላይ ያለው ወደ ታችኛው የአፈር ክፍል በመሄድ ሰብሎች ምግብ እንዳያገኙ በማድረግ ጉዳት ያስከትላል” ብለዋል፡፡
በቂ ዝናብ አለማግኘትና የአፈር አፈጣጠር በራሱ ለአሲዳማነት ተጋላጭ የሚያደርግ ሲሆን፤ አፈር ለሰብል ንጥረ ነገሮችን እና ውሃን መስጠት ሳይችል ሲቀር ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በተለይም የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት ወይም (ፒ ኤች) ከ7 በታች የሆነ እና የሀይድሮጅን እና አልሙኒየም (Al+3) ንጥረ ነገሮች የሚበዙበት አፈር አሲዳማ አፈር አፈር ተብሎ እንደሚጠራ አስረድተዋል፡፡
የአፈር አሲዳማነት በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትልና ምርትንም ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ የደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ቤንሻንጉል ክልሎች ለዚህ ችግር ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አሲዳማ አፈርን ለማከም እና በምርት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማስቀረት ላላፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከክልል ግብርና ቢሮዎች ጋራ በመሆን፤ ትኩረት ሰጠቶ ሰፊ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹም ሲሆን፤ “ለአብነትም በጋራ ከመስራት ጀምሮ የፖሊሲ ችግሮች እየተፈቱ ያለበት ሁኔታ አለ” ብለዋል፡፡
“በዓለም አቀፍ ደረጃ አሲዳማ አፈርን ለማከም እንደ መፍትሄ የሚወሰደው ኖራ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ኖራን በሚፈለገው ጊዜ እና መጠን መጠቀም ከተቻለ አሲዳማ አፈርን ከማከም በተጨማሪ ምርታማነትን እስከ 3 በመቶ መጨመር እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
በተያያዘም አሲዳማ አፈርን መቋቋም የሚችሉ አስር ዝርያዎች ስለመውጣታቸው የገለጹ ሲሆን፤ “እነዚህም የተሻለ ምርት የሚሰጡ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአፈር አሲዳማነት የንጥረ ነገሮች እጥረትን በማስከተል የሰብል ዕድገትን በማቀጨጭ በሰብል ምርት ላይ ከ50 በመቶ እስከ 100 በመቶ የሚደርስ የምርት ቅነሳ እንደሚያስከትል በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
አሐዱ ራዲዮ
