በአማራ ክልል ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ከእንስሳት ወደ ሰው ከሚተላለፉ በሽታዎች መካከል አንዱ በሆነው በአባሰንጋ በሽታ፤ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ከ2 ሺሕ በላይ ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት አስታውቋል።
ከሌሎች ጊዜያት አንጻር በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ፤ ሕብረተሰቡ እንስሳትን ክትባት አለማስከትብና እና ያልተመረመረ ስጋን መመገብ እንደሚገኙበት የኢንስቲትዩቱ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ የሙያተኞች ቡድን ሰብሳቢ ሐብታሙ አለባቸው ተናግረዋል።
አክለውም፤ በዋናነት ሕብረተሰቡ እንስሳትን ማስከተብ ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ሌላኛው ፈተና እንደሆነ አንስተዋል።
የበሽታውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ የቅድመ መከላከል ሥራዎች በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ከነዚህም ውስጥ ነዋሪዎቹ እንስሳትን እንዲያስከትቡ የማስተማር ሥራ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።
ኃላፊው አያይዘውም በዋናነት የበሽታው ተጠቂ ነዋሪው በመሆኑ፤ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ በነቂስ መሳተፍ እንዳለበት አሳስበዋል።
የአባሰንጋ በሽታ ባሲለስ አንትራሲስ በሚባል በሽታ አምጪ ተህዋስ አማካይነት የሚከሰትና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፤ የቤት እንስሳት በሆኑት የዳልጋ ከብት፣ በግ፣ ፍየል፣ የጋማ ከብትና አሳማ እንዲሁም የዱር እንስሳትም ላይ ይከሰታል።
በሽታ አምጪ ተህዋሱ ከእንስሳቶች በተለያየ መንገድ ወደ ሰው አካል ከገባ በኋላ ራሱን በማባዛትና በመላው የሰውነት ክፍል በመሰራጨት ለበሽታ እንደሚዳርግ ተመላክቷል፡፡
በበሽታው ከተበከለ የእንስሳት ስጋና የእንስሳት ውጤቶች ጋር በሚኖር ንክኪ በቆዳ ላይ በሚገኝ ቁስል ዘልቆ ሲገባ እንደሚከሰት የተገለጸም ሲሆን፤ በተጨማሪም ከአየር ላይ በትንፋሽ አማካኝነት ወደ ሳምባ ሲገባ እንዲሁም በአባሰንጋ በሽታ የተበከለ ጥሬ ሥጋ በመብላት ወደ ሰዎች ይተላለፋል፡፡
በዚህም ምክንያት በበሽታው የተጠቁ እንስሳት ካሉ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ሲሆን፤ እንስሳቶቹ በበሽታው መሞታቸው ከተረጋገጠ ደግሞ ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖር በማድረግ በጥንቃቄ መቅበር ወይንም ማቃጠል እንደሚገባም ተጠቁመዋል።
አሐዱ
