በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበረዉ የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል የንግሥ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ ከቁልቢ ከተማና አጎራባች የፀጥታ አካላት ጋር የገዳሙ ኀላፊዎች ዉይይት አካሄዱ።
በውይይቱ ወቅት በዓሉን ለማክበር ወደ ስፍራው ለሚጓዙ ምዕመናን በአስተማማኝ መልኩ ሰላምና ደህንነታቸዉ ስለሚጠበቅበት ሁኔታ ንግግር ተደርጓል።
ከዚሁ ጋር የትራፊክ ፍሰቱ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለሚኖራቸው ኀላፊነት ተነስቷል። በውይይትና ምክክሩ ላይ የፀጥታ ሥራው ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ ፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ፣ ከድሬደዋ ፖሊስ እንዲሁም ከሐረሪ ፖሊስ ጋር በጋራ በመቀናጀት እንደሚሠራም ተገልጿል።
ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ቀደም ሲል ለኢኦተቤ ቴቪ በስልክ በሰጡት አስተያየት፣ በዓሉ ያለምንም ጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በቂ ቅድመ ዝግጅት መካሄዱን መግለጻቸው ይታወሳል።
Via የመንበረ ፓትርያርክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
