በአዲስ አበባ ብቻ 500 ሺሕ የአከራይና ተከራይ ውል ተመዝግቧል

Date:

የአከራይና ተከራይ ውሉ ተፈፃሚ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ብቻ 500 ሺሕ የሚደርስ የአከራይና ተከራይ ውል መመዝገቡን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት የዋጋ ንረት በአግባቡ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር እንዲሁም፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው እና የአከራና ተከራይ መብቶችን ለማስተናገድ የሚያስችል የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጹት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢትዮጵያ በደቻ ናቸው።

በዚህ አዋጅ መሠረትም በ2017 በጀት ዓመት 283 ሺሕ 822 የኪራይ ውሎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ አዋጁ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጀምሮ ባለፈው ግንቦት ወር ድረስ በአጠቃላይ በመላ ሀገሪቱ ወደ 757 ሺሕ 623 ውሎች በአከራይና ተከራይ በኩል መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህም ውስጥ ወደ 500 ሺሕ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ የተመዘገበ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል 161 ሺሕ 807፣ በሲዳማ 20 ሺሕ 16 እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 26ሺሕ አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 23 ሺሕ ገደማ፣ በሀረሪ 5 ሺሕ 944፣ በደቡብ ኢትዮጵያ 18 ሺሕ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ደግሞ 814 የኪራይ ውሎች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

የአዋጁ መተግበር ከዚህ ቀደም ሲነሳ የነበረውን የአከራይና ተከራይ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ሕጋዊ አሰራር መፍጠር መቻሉን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚው፤ የአከራይንም ሆነ የተከራይን ጉዳይ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስተናገድ የቻለ ስለመሆኑ አንስተዋል። አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ስርዓትን በማስቀረት ለዜጎች እፎይታን መስጠት መቻሉንም አክለዋል።

ይህ አዋጅ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት አንስቶ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በየራሳቸው ለአዋጁ ማስፈፀሚያ የሚሆን ደንብና መመሪያ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተው፤ አዋጁ ጉዳዩን በማያስፈፅሙ አካላት ላይና የሚነሱ ቅሬታዎችን መመለስ የሚያስችል አሰራር መያዙን አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት ከአዋጁ በተጨማሪም በተቀመጡ ደንቦችና መመሪያዎች በአከራይና ተከራይ በኩል የሚነሳ ቅሬታ ካለ መፍታት የሚችሉ እንደሆነ ገልፀው ለዚህ የሚሆን መዋቅር ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ይህንን በተመለከተም አጠቃላይ የአዋጁ አተገባበር ያመጣውን ለውጥ ለማወቅ ባለፈው አንድ አመት ጥናት ሲካሄድበት መቆየቱን ገልፀው በቅርብ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...