ሚክሮን ሮቢንሰን ትባላለች። ባርቤዶሳዊት ጋዜጠኛ ነች። በወጣትነቷ ጥሩ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ናት። እዚህ ቬኔዝዌላ ካራካስ ከተማ በነበረ የጋዜጠኞች የልምድ ልውውጥ ላይ ከኢትዮጵያ የመጣሁ መሆኔ ሲነገር ወዲያው መጥታ አናገረችኝ። እራስዋን አስተዋወቀችኝ። ከዚያም እንዲህ አለችኝ:- “የአንተ ሀገር ኢትዮጵያ እና የኔ ሀገር ባርቤዶስ ትልቅ ታሪክ አላቸው” አለችኝ።
ምን አይነት ታሪክ? አልኳት።
“ባርቤዶሳዊያን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ውስጥ ሳሉ፣ ከዚያ መከራ ለመላቀቅ ወደ መጣንበት ኢትዮጵያ እንሂድ የሚባል እንቅስቃሴ ነበር” አለችኝ። ቀጠለች:- “እናም ሁሌ ስለ ኢትዮጵያ ማወቅ እፈልጋለሁ። አነባለሁ። በጣም ትልቅ ታሪክ ያለባት የጥቁር ምድር ነች። እናም በውስጤ ሀገራችን ናት የሚል ስሜት አለኝ። ኢትዮጵያዊ ማግኘት እፈልግ ነበር። ስላገኘሁክ ደስ ብሎኛል” አለችኝ። እኔም ደስታዋን አይቼ አቀፍኳት።
እንደውም ድሮ ከእኔ ሀገር ባርቤዶስ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው በራስ ተፈሪ Kings of king ዘመን ትምህርት ቤት ሰለከፈቱ ባልና ሚስት አንብቤያለሁ አለችኝ። ስማቸውን ለማስታወስ ጣራ ጣራውን አየች።
እንደምንም ብላ አንድ ስም ጠራች። “Minio”? ብላ ጠየቀችኝ።
አዎ ሚስ Minion-Lorranine-Innis Ford እና ባለቤታቸው Arnold Josiah Ford ናቸው አልኳት። እንደገና በደስታ አቀፈችኝ። ስላስታወስኳት ደስ አላት።
በነገራችን ላይ እነዚህ ሁለት ጥንዶች ከአመታት በፊት በሞት ያጣነው የፕሮፌሰር አቢይ ፎርድ ወላጆች ናቸው። ከ1920 ዓ.ም ከባርቤዶስ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው። የመጡበት ምክንያት የጥቁሮች መብት ተሟጋቹ ማርክስ ጋርቬይ በሰሜን አሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ እና በካሪቢያን ደሴቶች ላይ መከራ የሚያዩ ጥቁሮች ወደ ስረ መሰረታቸው አፍሪካ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ይቀሰቅስ ነበር።
የዚያን ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ መረጃ የሚሰጡት ሀኪም ወርቅነህ እሸቱ እና ዶክተር መላኩ በያን ነበሩ። ሀኪም ወርቅነህ ከመቅደላ አፄ ቴዎድሮስ ሲሰው በህፃንነታቸው፣ በሶስት አመታቸው አግኝተዋቸው ወደ እንግሊዝና ሕንድ ሀገር ወስደው ያስተማሯቸው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዶክተር ናቸው። በ1920 ዓ.ም ደግሞ የካሪቢያኗ የሄይቲ ሀገር የጤና ሚኒስትር ነበሩ።
ዶክተር መላኩ በያን ደግሞ በአሜሪካ ውስጥ ሕክምና ተምሮ የተመረቀ የመጀመሪያው ዶክተር ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ለጥቁሮች መብት ተሟጋቹ ማርክስ ጋርቬይ ስለ ራስ ተፈሪ እና ስለ ኢትዮጵያ ያስተማሩት ናቸው። እናም ጥቁሮች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ የሚለው ንቅናቄ ጅማሮው በዚህ ምክንያት ነበር። International Negro Movement Association
እናም ከባርቤዶስ የደሴት ሀገር ሚስስ Minion-Lorraine-Innis Ford እና ባለቤታቸው Arnold Josiah Ford ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ፕሮፌሰር አቢይ ፎርድንም የወለዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የአዲስ አበባ ልጅ የነበረው ወዳጄ መምህሬ አቢይ ፎርድ፣ ፈጣሪ ነፍሱን ይማራት።
እናቱ በአዲስ አበባ ከተማ የከፈቱት ትምህርት ቤት ስሙም ልዕልት ዘነበወርቅ ይባል ነበር። የተማሪዎች የስካውት ቡድንንም ያስጀመሩት እርሳቸው ናቸው። አባቱ Arnold Josiah Ford የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከፍተው ኢትዮጵያን በረቂቁ ሙዚቃና ባሕል ያዘመኑ ናቸው። ከባርቤዶስ የመጡ።
እነዚህ ጥንዶች ብዙ ያልተነገረላቸው የኢትዮጵያ ወዳጆች ነበሩ። ፋሽስቶችም ኢትዮጵያን ሲወሩ አርበኞች ነበሩ።
በካራካስ ከተማ ያገኘኋት ባርቤዶሳዊት ኢትዮጵያዊ ነኝ አለችኝ። በታሪክ። ተባረኪልኝ።
ከጥበቡ በለጠ f.b ገጽ
