በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈው የሚድያ ሰው ሙሉጌታ ገሰሰን ለማስታወስ “የሙሉጌታ ገሰሰ” አምድ በሚል የማስታወሻ ገፅ ይፋ መሆኑ ታወቀ፡፡
tewedajewikipedia.com .በተሰኘው የሕይወት ታሪኰች በሚሰነዱበት ድረ ገፅ ላይ አንደኛውን ክፍል የሙሉጌታ ገሰሰ አምድ ተብሎ መሰየሙን የተወዳጅ ሚድያ ማኔጅመንት አስታውቋል፡፡
የፋና መሥራችና የመጀመሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ ገሰሰ ሐምሌ 25 2017 ዓ.ም ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ፋና አሁን ለደረሰበት ደረጃ ና ጠንካራ የሥራ ስልት እንዲኖረው ያደረጉ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡
ፋና ሬድዮ ሲመሠረት አንስቶ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት የሚታወቁት ሙሉጌታ ገሰሰ ብዙዎችን ለሥራ የሚያነሳሳ የአመራር አካሄድ በመከተላቸው አድናቆት ለማትረፍ ችለዋል።
ተወዳጅ ሚድያ ፈር ቀዳጅ የሆኑ ባለሙያዎችን የማክበርና የማስታወስ ዓላማን የሰነቀ ድርጅት ሲሆን የሚድያ ሰው ሙሉጌታ ገሰሰን የሕይወት ታሪክ ከምስል ጋር በዲጂታል ሚድያዎች በማሰራጨት ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል።
እስከዛሬ የ 400 የሚድያ እና የጥበብ ሰዎችን ታሪክ በአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ መፅሐፍ ሰንዶ ያስቀመጠ ሲሆን የሙሉጌታ ገሰሰም በቀጣይ ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ ላይ የሚካተት ይሆናል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ የሥራ መሪ የሆኑት አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም ከ1987-1995 ለ ስምንት ዓመታት በፋና ያገለገሉ ሲሆን ለሙሉጌታ ገሰሰም ልዩ ቅርበት ያላቸው ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚናገሩት በሙሉጌታ ስም ፋና አንዱን ስቱዲዮውን ቢሰይም ጥሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሌሎችም ሙሉጌታን ለማስታወስ የራሳቸውን መንገድ ተጠቅመው ማስታወሻ ቢያደርጉለት ባለሙያው ምንጊዜም በትውልድ ልብ ውስጥ ሳይጠፋ እንደኖረ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ፣አገር ማለት የሰው ልጅ ነው ብሎ የሚያምን፣ እንዲሁም የሰዎች ታሪክ ተፅፎ መሰነድ የሚል መርህ ያነገበ ሲሆን “ታላላቆችን እናክብር” በሚልም ለባለሙያዎች ዕውቅና ይሰጣል፡፡
በመሆኑም፣ የሙሉጌታ ገሰሰ ቤተሰቦችን ፈቃድ በማግኘት የሙሉጌታ ገሰሰ አምድን ይፋ አድርጎታል።ይህ አምድ ከሙሉጌታ ገሰሰ ሥራና ሕይወት ጋር የተያያዙ ፅሑፎች የሚስተናገዱበት ሲሆን የፋና ትዝታዎችም የሚቀርቡበት ነው፡፡
በተጨማሪም ፣ከድረ ገፁ ጋር የሚያያዝ የፌስ ቡክ ገፅ የሚኖረው ሲሆን ሙሉጌታን በቅርበት የሚያውቁትም ሀሣቦችን በማቀበል ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
