በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅ ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሚሄዱ ተገልጋዮች ተሸከርካሪያቸውን ከዋና መንገድ ዳር ስለሚያቆሙ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የፓርኪንግ እና የመንገድ ትራፊክ መሰረተ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ጌታቸው ለኤፍኤም አዲስ 97.1 ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ የትራፊክ መጨናነቅን ለማቃለል ባለፈው ዓመት የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት ደንብ ቁጥር 165/2016 ማፅደቁ ይታወሳል፡፡
ደንቡን ተግባራዊ ለማድረግም በ11ዱ ክፍለ ከተሞች የህንፃ ስር የመኪና ማቆሚያን ለተለያዩ አገልግሎት ሲጠቀሙ የነበሩ 1 ሽህ 286 ህንፃዎችን በመለየት ስፍራውን ለተፈቀደለት አላማ እንዲያውሉ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በመንገድ ዳር የሚገኙ በጥናት የተለዩ 1ሽህ 227 ህንፃዎች ስር ያሉ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን በመለየት መንገድ ላይ ይቆሙና ከተማውን ያጨናንቁ የነበሩ ከ21 ሺህ 6 መቶ በላይ ተሽከርካሪዎች እንዲቆሙበተ ማድረግ ተችሏል ብለዋል አቶ ቢኒያም፡፡
የህንፃ ስር የተሸከርካሪ ማቆሚያውን አሁንም ለፑል ቤት፣ ለስቶር፣ ለጭፈራ ቤት፣ ለጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና ለሌላ አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉ 55 የህንፃ ባለቤቶች መቀጣታቸውንና ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
