በትግራይ ክልል ሽሬ እንዳሥላሴ ከተማ ከትናንት በስቲያ የጣለው ከባድ ዝናብ በተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ እና በከተማዋ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የሽሬ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ጎይትኦም ይስማኝ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
የመሞት አደጋ ለተጋረጠበት 250ሺህ ተፈናቃይ መፍትሔ ባለመሰጠቱ አሁን ላይ ችግሮች እየበዙ መሆኑን አንስተው “ይህ እየሆነ ያለውም የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎት ባለመኖሩ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አስተባባሪው በዝርዝር ምን አሉ?በከተማችን ነሀሴ 6/2017 ዓ.ም ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ በተለይ በተፈናቃዮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ተጠልለው የሚገኙበት ሁሉም መጠለያ በጎርፍ ተሞልቷል። ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ህብረት ትምህርት ቤት መጠለያ ካምፕ ክፉኛ ተጎድቷል።
በ18 መጠለያ ካምፖች ውስጥ ወደ 250 ሺህ ገደማ ተፈናቃዮች አሉ፣ ተሰጥቷቸው የነበረው መጠለያ ሸራ በንፋስ ተነቃቅሏል፣ ተቀዷልም። እቃቸውም በጎርፉ ተወስዷል፣ አንዳንድ የቀሩትም ተበላሽተዋል።
አሁን ላይ ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው፣ ከፍተኛ ዝናቡም እንደቀጠለ ነው። የተፈናቃዮች ቁጥር ከከተማዋ አቅም በላይ ስለሆነ ድጋፍ ለማድረግ አልቻልንም።
ከሁሉም መጠለያ ካምፖች ውስጥ በየቀኑ ከ50 በላይ ተፈናቃዮች እየሞቱ ነው። ያ ማለት በእያንዳንዱ መጠለያ ከ3 ሰው በላይ ይሞታል። የሚሞቱት ደግሞ በርሃብ እና በብርድ ነው።
ተፈናቃዮች ሲታመሙ የሚታከሙበት ገንዘብ የላቸውም፣ አማራጫቸው መሞትና መሞት ብቻ ነው። ይህ ቁጥር ቀደም ሲል በተደረገ ጥናት የተገኘ ነው፣ አሁን ላይ ግን አየር ንብረቱም ስለተቀያየረ ከእጥፍ በላይ ይሞታሉ ሲሉ ነው የገለፁት።
በቂ ምግብ፣ ጥራቱን የጠበቀ የመጠጥ ውሃ የላቸውም፣ ሲታመሙ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ አይችሉም፣ ምክንያቱም ገንዘብ የላቸውም።
በየቀኑ የከተማችን ነዋሪዎች እና ተፈናቃዮች ሰላማዊ ሰልፎች ይደረጋሉ፣ መግለጫዎችን እናወጣለን፣ ለሚዲያዎች እናሳውቃለን፣ ነገር ግን የክልሉ መንግስት ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ነው ብሎናል ነው ያሉን።
አሁን ላይ ችግሩ በተፈናቃዮች ዘንድ ብቻ አይደለም፣ ነዋሪውም እየተጎዳ ነው። የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ ነገሮች በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ላሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት እንድባባስ አድርጓል ሲሉ ገልፀዋል።
@TikvahethMagazine
