ይህ ቃለ ምልልስ ግንቦት 2011 ዓ.ም ከግዮን መጽሔት ያደረጉት ሲሆን ምንም ማስተካከያ ያልተደረገለት መሆኑን እናስታውቃለን ።
የመጨረሻ ክፍል
ግዮን፡- ሙስሊሙ በሀገር ደረጃ ሀገሩን ለማሳደግ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
ሐጂ ዑመር፡- በቅድሚያ ሃይማኖታዊ ተግባሩ ላይ ኃላፊነቱን በደንብ ሊወጣ ይገባል፡፡ መሠረቱ አላህን መፍራት ነው፡፡ ሰውዬው አላህን ሳይፈራ ሥልጣን ላይ የወጣ እንደሆነ የተበላሸ ሥነምግባር ስለሚኖረው በዳይና አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው የአስተዳደር ልምድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ማስተዳድረ ከራስ ይጀምራል፡፡ መንደርን፣ ሕዝብን፣ ሀገርን ይመለከታል፡፡
ሙስሊሙ ከምኒሊክ ወዲህ ውስጣዊ ጭቆና የበረታበት ነበር፡፡ በነቴዎድሮስና ዮሃንስ የነበረው ውጫዊ ጭቆና እና ጦርነት ከምኒሊክ ወዲህ የለም፡፡ ውስጣዊ ጭቆናው ጠ/ሚ/ር ዐቢይ እስኪመጡ ድረስ አለ፡፡ ለእሳቸው (ለጠ/ሚ/ር ዐቢይ) ምስክርነት እሰጣለሁ፡፡ እኔ መቼም ለአላህ እንጂ ለሰው የምሰጠው ምስጋና የለም፤ ሰው ብዙም ሳያቆየው ያፈርሰዋል፡፡ ሰውን የሚያስከብር የሚያስሞግሰው፣የሚያዋርደውም ሥራው ነው፡፡ እሳቸው ከመጡ ወዲህ ሙስሊሙ ከአሁኑ የተሻለ ሰዓት ያገኛል የሚል እምነት የለኝም፡ በትክክል ከተሄደ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰውዬ ወደፊት ይመጣል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ ሙስሊሙ ከዚህ ቀደም ያላገኘውን ነው ያገኘው፡፡
“አንድ ሁኑ ተዋደዱ፣ የምትፈልጉትን አደርግላችኋለሁ” የሚል ጥሩ የሀገር መሪ አግኝተናል፤ከዚህ በፊተር እንዲህ ዓይነት ቅን ሰው ተገኝቶ አያውቅም፡፡ የበፊቶቹ ያለንን ሲወስዱብን ነው የኖሩት፤ የምናውቀውም ይህንኑ ነው፡፡ የነሱን መጥፎ ተግባር አሁን መተንተን ጸያፍ ነው፡፡ በጠ/ሚ/ር ዐቢይ ግን ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ይህንን መሪ ተባብሮ ካልደገፈይጸጸታል፤ እድለቢስ ይሆናል፡፡
ሙስሊሙ ከመንግስት ጎን ቆሞ ሃይማኖቱን፣ ሀገሩን መጠበቅ፡፡ እራሱን ማሳደግ አቋሙን ማስተካከል አለበት፡፡ አለዚያ ይሄ እድል ካመለጠ፣ ዳግም ይገኛል ብዬ አላምንም፡፡
ግዮን፡-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች በኢትዮጵያ ሙስሊም ስም የሚንቀሳቀስ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊምን ችግርም ጥያቄም የማይፈታ መብትም የማያስከብር ተቋም ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን እናንተ በአዲስ ልታዋቅሩ ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የራቀውን ሕዝብ፣ የመሰብሰብ አቅም አላችሁ? ሕዝቡስ ይመለሳል ብላችሁ ታስባላችሁ?
ሐጂ ዑመር፡- እኛ የማቀራረብ ሥራን አልጀመርንም፤ ለውጡ እስከታች አልወረደም፡፡ ጠቅላይ ም/ቤቱ ላይ ብቻ ነው የተንጠለጠለው፡፡ ወደ ወረዳ፣ወደ ክልል ገና አልወረደም፡፡ ሕዝቡን የሚያስወድደው ሥራችን ነው፡፡ እኛ ራስ ወደድ፣ ጥቅም ፈላጊ ከሆንን ህዝብ አያከብረንም፡፡ ለሕዝብ ከራሳችን ከቤተሰባችን ጉዳይ በላይ አስበልጠን መሥራት አለብን፡፡ ሕዝብ ሊከበር፣ ሊወደድ፣ ሊሠራለት ይገባል፡፡
ሕዝብን አገልጋይ መሆን ነው ስልጣን መያዝ፤ ይሄ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሕዝብን ካላቀፍን፣ ከሕዝብ ጋር አንድነት ካልፈጠርን ሥልጣን ላይ መኖር አንችልም፡፡ ከሠራንለት ሕዝቡን ወደኛ እናመጣዋለን፡፡ እስከዛሬ መጅሊስ ይመረጥ የነበረው ገንዘብ የሚፈልግ ነበር ማለት ይቻላል፤ ሁሉም ባይሆን፡፡
ድህነቱ ወደሥልጣን ያመጣው ገንዘብን ሲያይ አያስችለውም፡፡ በሥልጣኑ የሚኖር ጥቅም የሚፈልግ ሕዝቡን ንቆ ሥልጣኑን ወደሚያቆይለት አካል ፊቱን ያዞራል፡፡ እኛ ይህንን ጠንቅቀን ተረድተን ነው ወደዚህ የመጣነው፡፡ ሰፊው ሕዝብ ከኛ ይርቃል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ግዮን፡-የቀድሞ መጅሊስ መንግሥትን ሙጥኝ ያለ ነበር፡፡ እናንተ ደግሞ በመንግሥትና በሕዝብ መሐል ድልድይ ናችሁ፡፡ ይህ መንግሥት የሚባል አካል በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ በተለያየ ጊዜና በተለያየ ሁኔታ እጁን እያስገባ ያለ አይመስሎትም?
ሐጂ ዑመር፡- የእስከዛሬው ከሕዝብም ከመንግሥትም አንድ የሆነ አልነበረም፣ ታዛዥ አሽከር ነበር፡፡ የመንግሥት አካል ነኝ የሚሉ ሰዎች ነበሩ መጅሊሱን ያሽከረክሩት የነበሩት፡፡ እኛ መንግሥት የሚያዘውን ሁሉ ለመሥራት አይደለም የተቀመጥነው፡፡ መደገፍ ያለበትን እንደግፋለን፡፡ ሕዝብን በሀገራዊ ጉዳይ እናሳትፋለን፡፡ ሕዝብ ለሀገሩ እንዲሰራ እናደርጋለን፡፡ የሕዝብን መብት መንግሥት እንዲያከብር እናደርጋለን፡፡ ይህ ካልሆነ እዚህ ጋ መቀመጣችን ምን ፋይዳ አለው?
ግዮን፡-ለኢትዮጵያ ሙስሊም መንግሥት የገባላችሁ ቃል ምንድነው?
ሐጂ ዑመር፡-በ1966 ሚያዝያ ሙስሊሙ ለመንግሥት 13 ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ በወቅቱ የጃንሆይን መንግስት በመቃወም አደባባይ ወጥቶ ነበር፡፡ 13ቱ ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ነበሩ፡፡
1.የእስልምና ሃይማኖት የመንግሥት ድጋፍ እንዲኖረው፤ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ይስፈር
2.ኢትዮጵያውያን እስላሞች በእስልምና ሃይማኖት የሊቃውንት ጉባኤ በጠቅላላውም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መራጭነት የእስልምና መሪዎች፣ ሙፍቲዎችናረዳቶች የመንፈሳውያን ጉዳዮች እንዲመሩ ይጽደቅልን
3.የሸሪዓ ፍርድ ቤት በ1936 በቁጥር 62 በወጣው አዋጅ ለዘመናት ሲሰራበት ቆይቶ ባላወቅነው ምክንያት በፍትሀብሔር አንቀጽ ሕግ ቁጥር 33447 ንዑስ ቁጥር አንድ በመለወጡ፤ አሰራሩም የሕግ ድጋፍ የተነፈገው ስለሆነ በአዲስ መልክ እንዲወጣልን
4.የእስላም ሃይማኖት ተከታዮች በዓላት የሕዝብ በዓላት ሆነው እንዲከበሩ
5.የወጣት ወንዶችና የወጣት ሴቶች ማኅበራት እንድናቋቁም ይታወጅልን
6.የመሬት ሥሪት ይሻሻል፡፡ ሙስሊሞች መሬት እንዳይኖራቸው በአንዳንድ ክፍለሃገሮች እየተደረገ በመሆኑ፡፡
7.የላይኛውን ያጸናል
8.እኛ ኢትዮጵያውያን እስላሞች በመንግሥት ሥራ በመሳተፍ ለውዲቱ አገራችን ያለንን የሥራ ድርሻ እንድናበረክት አዲሱ ካቢኔ ጥብቅ እርምጃ እንዲውስድልን እንጠይቃለን፡፡
9.ለእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግልን
10.በሬዲዮና ቴሌቪዥን ልክ ለክርስትና እንደሚፈቀደው የእስልምና እምነት ስብከት እንዲደርግ ይፈቀድልን
11.”በኢትዮጵያ የሚገኙ እስላሞች” እየተባለ በሬድዮም ሆነ በቴሌቪዥን በማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች የሚነገረው አነጋገር ቀርቶ “ኢትዮፕያውያን እስላሞች” ተብሎ እንዲነገር
12.የሃይማኖት ትምህርት በካሪኩለም ገብቶ ስለሚሰጥ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርትም በካሪኩለም ውስጥ ገብቶ.እንዲሰጥልን እንፈልጋለን፡፡
13.መንግሥት በመላ ኢትዮጵያ መስጊዶች የሚሰሩባቸው ቦታዎች መስጊድ ሠርተቶ ከነመተዳደሪያቸው እንዲያደራጅልን እንለምናለን.የመስጊድ እቃዎች ከውጭ ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ እንጠይቃለን
(ውድ አንባብያን የዚህን 13 ነጥብ በተሟላ ሁኔታ ለማግኘት 3ቱ አጼዎች የአህመዲን ጀበል መጽሐፍ ይመልከቱ ይህ ቁንጽል ነው – የጽሑፉ አዘጋጅ)
በዛን ዘመን እነዚህን 13ቱን ጥያቄ ስናቀርብ ክርስቲያኑም ከጎናችን ነበር፤ ተዓምር የሆነ ሰልፍ ነበር ያደረግነው፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ እኔም ነበርኩ፡፡ ደርግ ከ13ቱ ሦስቱን መለሰ፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ከ13ቱ 12ቱን መልሷል፡፡ ኢህአዴግን የኢድ-አደባባይ እንዲሰጠን ጠይቀን፤ አሸዋ ሜዳ መውጫ አካባቢ 175ሺካሬ ሜትር ከ20 ዓመት በፊት ሰጥቶን ነበር፡፡ የመጅሊሱ ደካማ መሆን መሬታችንን አስወሰደ፡፡ ሙስሊሙ በየጊዜው መብቱን ከመጠየቅ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ የሸሪአ ፍርድ ቤትም ሌላው ችግር ነበር፡፡
አሁን ሦስት ነገሮችን ነው የጠየቅነው፡፡ አንደኛው መጅሊሱ በአዋጅ እንዲቋቋም መጠይቅ ነው እንደ ጓደኞቻችን፡፡ ሕጉን አርቅቀን አስገብተናል፣ ሌላው ሸሪዓ ፍርድ ቤት ጉዳይ ነው፡፡ እሱንም እንደሚያስተካክል ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ቃል ገብተውልናል፡፡ ሌላው እሰላማዊ ባንክ ነው፤ እሱን ለማቋቋም “እናንተ አንድ ከሆናችሁ ይቀቋቋማል፤ ካልሆናችሁ ከእናንተ አይደለሁም” ብለውናል ጠ/ሚ/ሩ፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ነው ያለነው
ግዮን፡- ሐጂ ከእርስዎ ጋር የነበረን ቆይታ ከማጠናቀቃችን በፊት፤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትዎን በዚህ አጋጣሚ ይስጡን?
ሐጂ ዑመር፡- ለመላው የኢትዮጵያ ሙስሊም እንኳን ለ1440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፡፡ እንኳን ረመዳናችሁን በሰላም ጨረሳችሁ፡፡ አደራ የምላችሁ ለሙስሊሙም፣ ለክርስቲያኑም ሰላማዊ አካሄድ እንሂድ ፣ሰላማችንን እንጠብቅ ፣እንረዳዳ፣ አገራችንን እንውደድ ፣መሪያችንን እንርዳ፣ እንመካከር፡፡ ሁላችንም በጋራ ለኢትዮጵያችን እደገት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደግ እላለሁ፡፡
ግዮን፡-እናመሰግናለን፡፡
