የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቀድሞ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል እና ልጃቸው ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል።
አቶ ምትኩ ካሳ በኮሚሽነርነት ዘመናቸው የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን የተለያዩ የእርዳታ ዓይነቶችን ከመጋዘን ወጪ በማድረግ ለተረጂዎች ሳይደርስ እንዲሸጥ በማድረግ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉ ተገልጿል።
ክሱ እንደሚያብራራው፣ ኮሚሽነሩ ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዳይሬክተር ከማነ ወ/ማሪያም እና ከሌሎች ሰራተኞች ጋር ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር፣ በሺዎች በሚቆጠሩ ተረጂዎች ስም የምግብ ቁሳቁሶችን ከኮሚሽኑ መጋዘን አውጥተዋል።
በዚህም ምክንያት በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና የደቡብ ክልል (የቀድሞ) ክልሎች በሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅቱ ማዕከላት የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ከኮሚሽኑ የወጡ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ተሽጠው ለግል ጥቅም መዋላቸው በክሱ ተመላክቷል።
በተለይም 601 ሺህ 668 ኩንታል ስንዴ፣ 41 ሺህ 789 ኩንታል በቆሎ፣ ከ78 ሺህ ሊትር በላይ ዘይትና 3,999 ኩንታል ሩዝ ከተራድኦ ድርጅቱ ጋር በመመሳጠር አዳማ ለሚገኝ የዱቄት ፋብሪካ መሸጡ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በሁለተኛ ክስ 472 ሚሊየን 886 ሺህ 304 ብር በድጋፍ መልክ በመውጣት ለግል ጥቅም በመዋል በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ መድረሱን ተገልጿ።
አቶ ምትኩ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን በተመለከተ ደግሞ በስማቸው ተገዝተው የተገኙ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል የየራሳቸው ተሳትፎ እንደነበራቸው በክሱ ተዘርዝሮ ነበር።
