ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ1960ዎቹ ከቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ድል ወዲህ ሁለተኛው ድል ነው ሲሉ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትብብር ለማሳደግ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ያሉት ላውረንስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባት አስደናቂ ስኬት ተቀዳጅታለች ብለዋል፡፡
ግድቡን ሁለት ጊዜ የመጎብኘት ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ግድቡ የጋራ ትብብርን ከማሳደግ ውጪ ሌሎች ሀገራት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመሆን ግድቡ እንዳይገደብ የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም ችለዋልም ነው ያሉት፡፡
አክለውም ”የግብጽ መሪዎች ከትብብር ይልቅ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ያራምዳሉ” ያሉ ሲሆን፤ በዚህም ዓባይን በጋራ አልምቶ ከመጠቀም ይልቅ ኢትዮጵያን በጠላትነት ይፈርጃሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ በቀጠናው የሚያደርሰው ጉዳት ባይኖርም፤ ግብጾች ”ኢትዮጵያ ጠንካራ ከሆነች ሀገራችን ደካማ ትሆናለች” የሚል የተሳሳተ ግምት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
ግብጽ ሁሌም በጂኦ-ፖለቲካ የበላይ የመሆን አመለካከት አላት፤ ይሄም በጋራ ለማደግ ከባድ እንቅፋት ከመሆን ያለፈ ጥቅም አልባ መሆኑን አንስተዋል።
ጋዜጣ ፕላስ
