የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፉት ወራት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን ከማደራጀት ጀምሮ በምርጫ ክልሎች የምርጫ ጣቢያ ጽሕፈት ቤቶች የመክፈት ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውቋል።
የምርጫ ጣቢያዎች ለምርጫ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ የቦርዱ ባለሙያዎች በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘትና በመዘዋወር ምርጫ ጣቢያዎች፤ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለሴቶች፣ ለአረጋውያን ምቹ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራ በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ሰርተዋል ሲሉ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሕዝቡ ወጥተው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸውን በመገናኛ ብዙሃን ለሕዝቡ ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ይህንን ማድረግ የሚያስችላቸው ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
ከስልጠናም በተጨማሪም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሙከራ ክርክር እንዳደረጉ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ገልጸው፤ በዚህም ወደ 56 የሚሆኑ ፓርቲዎች በተመረጡ 16 ርዕሶች ላይ ክርክር አድርገዋል ብለዋል።
በቀጣይ ወደ ሕዝብ ወጥተው የየራሳቸውን ፕሮግራም የሚያቀርቡ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
ቦርዱ የ7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል። በሌላ በኩል የምረጡኝ ቅስቀሳው ከጥር 5 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፤ ቅስቀሳ ማድረግ የማይቻልበት የጽሞና ጊዜ ደግሞ፤ ከግንቦት 20 እስከ ግንቦት 23 ቀን ድረስ ነው ተብሏል።
አሐዱ ራዲዮ
