የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የመስክ ምልከታ አድርጓል።
ቋሚ ኮሚቴው የኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ፣ የተገኙ ውጤቶች፣ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እና መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ከተቋሙ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፣ ኢንስቲትዩቱ እያደገ መምጣቱን ገልፀው የትስስር አዋጁን መሰረት አድርጎ ሥራዎችን መተግበር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ጥራቱን የጠበቀና ሀገራዊ የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎቱን ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልፀው፣ ይህን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ብሩክ ከድር በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ አሰልጣኝ መምህራንን ከማፍራት፣ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂና የምርምር ሥራዎችን ከመሥራትና የፓሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ከማቅረብ አኳያ ግዙፍ ተልዕኮ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ኢንስቲትዪቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም አዋጅ የሚመራ ቢሆንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሠራተኛውን የሚመለከቱ ጥቅማ ጥቅሞች በሙሉ ለኢንስቲትዩቲ እንደማይደርሱም ገልፀዋል።
ለሰለጠነ የሰው ሀይል አቅርቦቱ ትርጉም ያለው ሚና የሚጫወቱት አሰልጣኝ መምህራን መሆናቸውን ገልፀው፣ ቋሚ ኮሚቴው ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠውና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት ችግሩ እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የትስስር አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ኢንስቲትዪቱ ከ150 ኢንዱስትሪዎች ጋር ስምምነት ጭምር ተፈራርሞ እየሠራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ስልጠናን ከተግባር ጋር ለማስተሳሰር እና የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ ኢንተርፕራይዝ በመመስረት ተኪ ምርቶችን በማምረት የሀገራችንን ልማት ሥራዎች የሚደግፉ ተግባራትንም እያከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል።
በዋና ግቢና በሳተላይት ካንፓሶቹ ከ8 ሺህ በላይ ሰልጣኞች እና 400 መምህራን እንዳሉት የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአሰልጣኞቹን ፕሮፋይልን ለማሣደግ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እየሠራ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል።
