‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› የተሰኘው መጽሐፍ ተመረቀ

Date:


አሁን በሥራ ላይ ባለው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የማሻሻያ ሐሳቦችና ምክንያቶቹ ላይ መሠረት ተደርጎ በቀድሞ ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል የተጻፈው ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› የተሰኘው መጽሐፍ የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እሸቱ ጮሌ አዳራሽ በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት ተመርቋል፡፡

በመድረኩ ፀሐፊው አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል ቅድመ 1997 ዓ.ም የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት የሕግ አማካሪ እና በኋላም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ በመኾን ማገልገላቸው፣ በብዙዎች የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ትውስታ ውስጥ አይረሴ በኾነው የ1997 ዓ.ም ምርጫ ከ200 በላይ የሚኾኑ ዜጎች ላይ የግድያ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ በወቅቱ ኹነቱን እንዲያጣራ የተቋቋመውን ኮሚቴ በሰብሳቢነት መርተው ሀገርና ፍትሕ የጣለችባቸውን አደራ በሚገባ የተወጡ መኾናቸው ተወስቷል፡፡


ፀሐፊው ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት ሕልውና አደጋ ውስጥ የገባባቸው ችግሮች በእጅጉ ያሳስባቸው ስለነበር፣ ያላቸውን የሙያና የሕይወት ተሞክሮ ዋቢ በማድረግም መጽሐፉን ለማዘጋጀት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› የሚል ርዕስ የተሰጠው መጽሐፉ፣ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የገባችበትን የሁለት ወገን ፖለቲካዊ ፍላጎትና ርዕይ ለማስታረቅና ወደ መሀል ለማምጣት፣ ሕገ መንግሥታዊና መዋቅራዊ ችግሮችንና በጎ መልኮችን ከመሠረቱ ለመፈተሽ የሚሞክር መኾኑ ተገልጽዋል፡፡


መጽሐፉ በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥታዊነት ባሕል እጦት ያመጣውን ፈተና በጥልቀት ከመመርመር አንስቶም፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ችግር፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት ስብጥር በሒደት አናሳ ብሔረሰቦችን ሚና የሚያሳንስ መኾኑ፣ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ስንት ይሁን? የክልሎች አወቃቀር በምን መልክ ይሁን? ስለመገንጠል መብት፣ የሕገ መንግሥቱ ባለቤትነት ችግር፣ ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት?…. በሚሉና በአሁኑ ወቅት ማሻሻያን የሚፈልጉ 16 ያህል ወሣኝ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ለማብራራትና ምክረ ሐሳቦችን ለማስቀመጥ የሚጥር መኾኑ ተነግሯል፡፡        

  
በመድረኩ የኢትዮጵያ ሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ፕ/ር መስፍን አርአያ፣ ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ አሥራት፣ የቀድሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና ደራሲ ሙሉጌታ አረጋዊን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ተገኝተው በመጽሐፉ ላይ አስተያየቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡

መጽሐፉ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየገባችበት ላለው ሀገራዊ የምክክር ሒደት አያሌ ጠቃሚ ሐሳቦችና ግብዓቶች ያሉት ስለመኾኑ የተነገረ ሲኾን፣ ጸሐፊው በባሕር ማዶ እየኖሩ ወገንተኛ ባልኾነ አተያይ የሀገሪቱን መሠረታዊ የፖለቲካ ተቃርኖዎች ፈትሸው ይኽንን ትልቅ ሰነድ ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው በማበርከታቸውም አድናቆትና ምሥጋና ተችሯቸዋል፡፡

ፀሐፊው አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤልም መጽሐፉ ከዚህ በኋላ የእሳቸው ሳይኾን የሕዝብ መኾኑን ገልጸው፣ ከሚያገኟቸው ጠቃሚ ሐሳቦችና አስተያየቶች ተነስተውም ተጨማሪ አተያዮችን አካትተው በቀጣይ ለማሳተም እንደሚሞክሩ ተናግረዋል፡፡ 


‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› የተሰኘው ይኽ የቀድሞ ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል መጽሐፍ ዋቢ ክፍሉን ጨምሮ በ282 ያህል ገጾች የተዋቀረ ሲኾን፣ ለገበያ የቀረበውም በ950 የኢትዮጵያ ብር፣ ከሀገር ውጪ ለሚኖሩ ደግሞ በ30 የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 229 የካቲት 14 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት...