በዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ሁለት መነኮሳት ሲገደሉ አንድ ረድዕ ቆስለዋል

Date:

በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በአድርቃይ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም በ480 ዓ.ዓ እንደተመሠረተ የሚነገርግለት ነው።

በገዳሙም ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 700 የሚጠጉ ገዳማውያን መነኮሳት ይኖራሉ።

ለማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ጣቢያ በደረሰው መረጃ መሰረት በገዳሙ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ታጣቂ ግለሰብ ከግብር አበሮቹ ጋር በመሆን በከፈተው የተኩስ እሩምታ የገዳሙ መነኮሳት መገደላቸው ታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት አባ ወልደ ሰንበትና አባ ወልደ ትንሣኤ የተባሉ መነኮሳት ወዲያው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን አባ ገብረ ማርያም የተባሉት ረድዕ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው በዛሬማ ከተማ በሕክምና ላይ መሆናቸውን የመረጃ ምንጫችን ነግረውናል።

የተገደሉት መነኮሳት ሥርዓተ ቀብራቸው በዕለቱ በገዳሙ ሥርዓት መሰረት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
የገዳሙ አባቶች በገዳሙ አጠገብ የዳጉሳ አውድማ ጥለው ባሉበት ወቅት ታጣቂ ግለሰብ አውድማው ድረስ በመምጣት “ከቤተ እግዚአብሔር አግብታችሁ ምግብ አብሉኝ” ብሎ መጠየቁ ለተኩሱ መነሻ መሆኑን በመረጃው ላይ ተነስቷል።

ነገር ግን ለሥራው የተመደቡ አባቶች “ከእንግዳ ማረፊያ ቤት ሆነህ መመግብ ትችላለህ፣ መነኩሴ ስላልሆንክ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መግባት ግን አትችልም ምክንያቱም ሥርዓተ ገዳሙ አይፈቅድልህም” እንዳሉት በደረሰን መረጃ ለማወቅ ችለናል።

ግለሰቡ በዚህም ተበሳጭቶ ለመተኮስ ሲሞክር “በሱባኤ ወቅት ግጭት መፍጠር አያስፈልግም” ብለው መነኮሳቱ ቢመክሩትም ገዳዩ ግለሰብ ስልክ ደውሎ አምስት ግብር አበሮቹን በመጥራት የተኩስ እሩምታ መክፈታቸውን ምንጫችን አስረድተዋል።

የመረጃ ምንጫችን እንደነገሩን ከሆነ ከዚህ በፊት ግለሰቡ ጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም አንድ የቅዳሴ ተማሪ አግኝቶ በመውሰድ ለማስለቀቂያ ከቤተሰቦቹ 200 ሺሕ ብር ከተቀበለ በኋላ ደቀ መዝሙሩን ገድሎት መገኘቱ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በወርኃ ጥቅምት 2018 ዓ.ም ከዳባት ወረዳ ለቀብር ወደ ገዳሙ የመጡ ምእመናንን ገዳዩ አግቶ 700 ሺሕ ብር ቢጠይቅም በሽምግልና ሊለቃቸው መቻሉን ከመረጃ ምንጫችን ለማወቅ ተችሏል።
በተመሳሳይም በጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም በማይ ደንጎላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ጊዮርጊዮስ ስባረ አጽሙ በዓል ተከብሮ ዑደት በሚደረግበት ጊዜ ተኩስ ከፍቶ ዑደቱ ተቋርጦ ታቦተ ሕጉ ወደ መንበሩ መመለሱን ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት ምንም አይነት የመንግሥት የፀጥታ አካላት በገዳሙ አካባቢ ባለመኖራቸው በመነኮሳቱ ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት መፈጠሩን የመረጃ ምንጫችን ገልጸውልናል፡፡

(EOTCMK TV )

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...

ከ 50 ሚሊዮን በላይ መራጮች በማንዋልና በዲጂታል ተመዝግበዋል

ከየካቲት 28_መጋቢት 28 የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል። በተለያዩ ጉዳዮች...