የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በማዕከላዊ ኢራን የአየር ክልል ውስጥ ሲበር የነበረ የአሜሪካ F-35 ተዋጊ ጄት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከባድ ጉዳት ማድረሱን አስታወቀ ።ቀ
እንደ አብዮታዊ ዘቡ ገለጻ፤ አውሮፕላኑ ያለበተ ሁኔታ እስካሁን እንዳልታወቀና ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ጠቅሶ ተከስክሶ ሊሆን የሚችልበት ከፍተኛ ዕድል እንዳለ ጠቁሟል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው ከ125 በላይ የሚሆኑ የአሜሪካ እና የእስራኤል ድሮኖችን በተሳካ ሁኔታ ካከሸፍን በኋላ ነው ያለው የኢራን ጦር፣ ድርጊቱ የሀገሪቱን የተቀናጀ የአየር መከላከያ ሥርዓት መሻሻልና ጥንካሬ የሚያሳይ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
አሜሪካና እስራኤል በጋራ በመሆን በፈረንጆቹ የካቲት 28 ፣2026 በኢራን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ መካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ውጥረት ውስጥ ወድቋል።
እስካሁን ሁለንተናዊ መሪውን አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ጨምሮ ከ1,300 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል።
ኢራን ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እስራኤልን፣ ዮርዳኖስን፣ ኢራቅን እና የአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎች ያሉባቸውን የባህረ ሰላጤው ሀገራት በድሮንና በሚሳይል እየደበደበችም ትገኛለች።
ይህም በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ከመሆኑም በላይ፣ የዓለም አቀፍ የንግድ ገበያን እና የአቪዬሽን እንቅስቃሴን እያስተጓጎለ ቀጥሏል። አናዶሉ እንደዘገበው::
