የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የኻርግ ደሴት ላይ ሊሰነዘር የነበረው ጥቃት በድንገት ‘እንደተገታ’ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ ቀደም ሲል ኢራንን “ክፉኛ እንመታለን” ብለው ቢዝቱም፣ አሁን ግን ከኢራን ጋር የሚደረገው ውይይት ትልቅ መሻሻል ማሳየቱንና በዚህ ሳምንት አውሮፓ ውስጥ ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ገልጸዋል።
ይህ ስምምነት ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት የሚያግድና የሆርሙዝ ወሽመጥ በአፋጣኝ እንዲከፈት የሚያስገድድ እንደሚሆንም ትራምፕ አረጋግጠዋል። ይህንን ተከትሎም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ መቀነሱ ታውቋል።
በሌላ በኩል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የአሜሪካን አቋም ያስተባበሉ ሲሆን፣ አሜሪካ በድርድሩ ላይ “ከልክ ያለፈ ጥያቄ” እያቀረበች በመሆኑ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቃረባቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱን አገራት ለማሸማገልና ውጥረቱን ለማርገብ ኳታር ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገች መሆኑ ተጠቁሟል።
