ሁለገቧ አርቲስት አለምጸሐይ በቀለ

Date:

ግርም ይለኛል። እውቀት ስናባክን። ያውም መስራት የሚፍልግን ሙያተኛ አይተን እንዳላየን ስንሆን።
እርግጠኛ ነኝ ያቺ ቁርጧ ቀን መጥታ ስናጣት የማንዘከዝከው እውነት የለም። እውቀቷን አይተን እንዳላየን ያለፍን ሁሉ ከአበባ ጉንጉኑ በላይ ምስክርነታችን ማብቂያ አይኖረውም።

አለምዬ በአንድ ወቅት ስትናገር እንደስማሁት “የት እንዳለሁ ያውቃሉ። ግን አይጠሩኝም!” ይህ ነው የኛ ችግር። ፋኖሶቻችንን ያለመጠቀም አባዜ። እዚህ ጋ የአርቲስት ስዩም ተፈራ አባባል ቦታው ነው። “በፍሬነት ዘመናችን ነው የምንተወው! ዘር መስጫ ሰዓታችን ላይ!” ይህ የብዙዎች እጣ ነው። ዘርን የማባዛት ችግር።

አንጋፋዋ አርቲስት፣ የራስ ቴአትሯ፣ ሁለገቧ ባለሙያ አለምጸሐይ በቀለ የት ትሆን ያለችው ብለን ጠይቀን እናውቃለን!? ሌሎችንም።
ግርም ካለኝ ውስጥ አንጋፋዋን አርቲስት አለምዬን ዘመናዊው ድረገጽ እንኳን አያውቃትም።

ስሟን ስትጽፉለት “ስለአለምጸሐይ የቀርበ መረጃ የለም!” ይልና ሌሎች ሞክሼዎቿን ያሳያችኋል። ቴአትር ለመስራት 4 ብር የእራት እየተሰጣቸው እያደሩ ቴአትርን ከተመልካች ጋ ካገናኙት ውስጥ አንዷን አለምጸሐይን ማኀበራዊ ድረ ገጽ አላውቃትም ሲል ያስቆጫል።

ይህ በዙሪያዋ ያሉ ሙያተኞችም፣ ጋዜጠኞችም ስለአንጋፋዋ ዝም፣ ጭጭ እንዳሉ ጠቋሚ ነው። እራሷም ስለራስዋ ዝምታ ውስጥ እንዳለች ማሳያ ነው።


አለምዬ በዝግጅትም ይሁን በትወና ደረጃ አንድ ከሚባሉት ውስጥ ነች። አስቡት እነ”የመሐን ቱሩፋት”ን፣ “ቁርጥ ቀን”ን፣ “ወንድ አይገባም”ን “ወርቃማ ፈሬ”ን ሌሎችንም ቴአትሮች በዋና አዘጋጅነት ፣ በረዳት ደግሞ ትዝ የሚለኝ “የአንድ ቀን እስረኞች”፣ “የአና ማስታወሻ”…በዛ ያሉትን ያዘጋጀች ነች። ያውም በመደበኛው የቴአትር ቤት መድረክ።


በተከታታይ ቲቪ ድራማም “ፎዚያ” አይረሴ ነው። “ቅብብል” የተሰኘውም የአለምዬ ዝግጅት ነበር።
ፊልሙ ላይስ ቢሆን? በዋና አዘጋጅነት፣ በረዳት ፣ በስክሪን ፕሌይ፣ የራሷን አሻራ አሳርፋለች። “እንቆዻ”፣ “የሴም ወርቅ” ፣”ቀይ ስህተት” “ባለታክሲው” ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።


በትወና ራስ ቴአትር ከወጡ ቴአትሮች አብዛኛው ላይ ተሳትፋለች። ለመጥቀስ ያህል “ትንታግ” ፣ “አማጭ” ፣ “የቴዎድሮስ እንባ” ፣ “የዋርካው ስር ምኞት” ፣ “ሁለት ክፍል ግብዣ” ፣ “ላጤ” ፣ እና “በር” የተሰኘው ከብዙ ጥቂቱ ነው። “ገመና”ን ጨምሮ ብዙ ቲቪ ድራማ ላይም ትወናዋን በብቃት ስትወጣ አይተናታል።


ሁለገቧ አርቲስት በውብ ድምጿ “የውበት ወጥመድ” ፣ “ቆንጆዎቹ” እና “ስም የለሽ” የተሰኙ ልብ ወለድ መጽሐፎችን የተረከችልን ጸጋውን የተቸረች ሙያተኛ(professional) ነች።

አለምጸሐይን አለማሰብ ለሙያው ኪሳራ ነው። ቴአትር ቤቶች “ቴአትር አዘጋጂልን” ብለው ከካበተው እውቀቷ ሊያቋድሱን ይገባል።


የግል ፕሮዲዉሰሮችም ኃላፊነቷን በአግባቡ መወጣት የምትችለውን ባለሙያ በመጋበዝ ተከታታይ ቲቪ ድራማና ፊልሞች ላይ እውቀቷን ብትጠቀሙ በአንድ ድንጋይ ሁለት ፣ሶስት …ትመታላችሁ።


ጥበባዊ የትምህርት ተቋማትም “ስልጠና ስጪልን?” ብላችሁ ብትጠይቋት ከእዚህ በፊት ያደረገችው ነውና ተማሪዎቻችሁ ውጤታማ ይሆናሉ።

አለምዬ በምትወጂ ሙያ እንደገና ከፍ ብለሽ አይሽ ዘንድ ምኞቴ ነው። የምትወዷት፣ አድናቂዎቿ ፍቅራችሁን፣ ምስጋናችሁን አቅርቡላት። ወዳጄ ጌታቸው ወልዩ “ምስጋና አጥንት ያለመልማል” ይላልና።

ፎቶ ፦ አርቲስት አለምጸሐይ በቀለ (በስተግራ) እና አርቲስት (ጥብቅ ወዳጇ) አዳነች ወልደገብርኤል።

ውድነህ ክፍሌ (ታዋቂ ደራሲ፣ ጸሐፊ ተውኔት እና ዳይሬክተር )

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እስከ አምስት ዓመት እስራት የሚያስቀጡ የመረጃ ነጻነት አዋጅ ጸደቀ

ለ15 ዓመታት በስራ ላይ ከቆየው “የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት...

በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተላለፈ ማስጠንቀቂያ

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እየተከታተለና...

በበጀት አመቱ 22.9 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው

ከታቀደው 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ኩንታል እስካሁን  20...

በቬንዝዌላ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የ32 ሰዎች ህይወት አልፏል

በቬንዙዌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን 7.2 እና 7.5...