የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደንብ ቁጥር 204/2018 ላይ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ ሎጆች፣ ፔንሲዮኖች እና እንግዳ ማረፊያዎች ላይ አዲስ የ5% የመኝታ አገልግሎት ታክስ ጥሏል፡፡
ከሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋም ከመኝታ አገልግሎት ማዘጋጃቤታዊ ታክስ ለመጣል የወጣው ደንብ ላይ እንደተመለከተው፤ ተቋማቱ ከተጨማሪ እሴት ታክስ በፊት የመኝታ አገልግሎት ሰጥተው ከሚያገኙት ገቢ ላይ 5% እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።
ይህ ደንብ ተግባራዊ የተደረገው የከተማ አስተዳደሩ የገቢ አቅሙን ለማሳደግና መሰረተ ልማቶችን ለማሻሻል እንደሆነ ተገልጾአል።
የመኝታ አገልግሎት ሰጪዎች የክፍል ብዛታቸውንና የዋጋ ዝርዝራቸውን ለገቢዎች መስሪያ ቤት ማሳወቅ እንዳለባቸው ደንቡ ጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም የተጣለው የ5 በመቶ ታክስ የመኝታ አገልግሎትን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፤ እንደ ምግብ እና መጠጥ ያሉ ሌሎች አገልግሎቶችን እንደማይመለከት በ‹‹አዲስ ነጋሪ›› ላይ ታትሞ የወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በገቢዎች ቢሮ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ተመዝግበው መመዝገቢያ መሳሪያዎችን በመጠቀም ለመኝታ አገልግሎቱ ደረሰኝ መቁረጥ እንደሚጠበቅባቸው እና የተገልጋዮችን መረጃ ብቻ የሚይዝ ራሱን የቻለ መዝገብ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች ወርሃዊ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለባቸው የሚያዘው ደንቡ፣ የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች በየሩብ ዓመቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ያዛል።
የሰበሰበውን የ5 በመቶ ታክስ ወቅቱን ጠብቆ ገቢ የማያደርግ አገልሎት ሰጪ ወይም ሀሰተኛ መረጃ ያቀረበ ግብር ከፋይ በወንጀል እንደሚጠየቅ ተጠቅሷል። ክፍያውን ያዘገየ ተቋም ደግሞ የባንክ ወለድ እና ተጨማሪ 15 በመቶ ቅጣት እንደሚከፍል በደንቡ ተጠቅሷል፡፡
