በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል መስማማታቸውን፤ ነገር ግን ቀደም ሲል የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን ለኢራን እንዳረጋገጡላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ።
“የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ድርድሩን እንድንቀጥል ጠይቀውናል። እኛም ይህንን ለማድረግ ተስማምተናል” በማለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
አክለውም “ነገር ግን አሜሪካ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ማብቃቱን በማያሻማ ሁኔታ አሳውቃቸዋለች” ብለዋል።
ለወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ሁለቱ አገራት ከሳምንታት በፊት የመግባቢያ ስምምነት ደርሰው ግጭቱ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ካላፈው ማክሰኞ ጀምሮ አሜሪካ በከፈተችው ጥቃት ጦርነቱ ዳግም ተቀስቅሷል።
አሜሪካ እና ኢራን ድርድራቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን ትራምፕ ያሳወቁት ኳታር ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት አሸማጋዮችን ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ ወደ ቴህራን ከላከች በኋላ ነው።
አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሲኤንኤን እንደተናገሩት የትራምፕ አስተዳደር ስትራቴጂ በኢራን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ግጭቱ እንዳይባባስ ጋብ በማድረግ ለዲፕሎማሲያዊ ጥረት በር መክፈት ነው።
