የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ ያፈራቸው አንጋፋ መሪዎች በዓለም አቀፍ እና በአህጉራዊ መድረኮች ላይ ያላቸው ተፈላጊነት እና ተፅዕኖ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጎላ መጥቷል።
ከቀናት በፊት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ የፓኪስታን ብሔራዊ አየር መንገድን ወደ ግል ይዞታነት ያዛወረው አዲሱ ጥምረት የቀድሞውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምን አየር መንገዱን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩለት በእጩነት መርጧቸዋል።
በጉዳዩ ላይ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ብሉምበርግ እንደዘገበው፣ በኪሳራ ውስጥ የቆየውንና በቅርቡ ወደ ግል ይዞታነት የተሸጋገረውን የፓኪስታን አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ ለመረከብ የመጨረሻ ሂደቶችን እያጠናቀቀ የሚገኘው የአሪፍ ሀቢብ ኮንሰርቲየም፣ የአቶ ተወልደ ገብረማርያምን ሹመት በይፋ ለማሳወቅ ዝግጅቱን አጠናቋል።
አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በበላይነት በመሩባቸው 11 ዓመታት ውስጥ፣ አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ማዕከል በመነሳት አህጉሪቱን ከዓለም ጋር በማስተሳሰር ወደ አፍሪካ ትልቁና ትርፋማው አየር መንገድነት እንዲያድግ ያደረጉበት ስኬታማ የሥራ ታሪክ፣ ለፓኪስታን አየር መንገድ አዲስ ሕይወት ለመዝራት ለተነሳው አዲሱ ባለቤት ዋነኛ ምርጫ ሊያደርጋቸው ችሏል።
እ.ኤ.አ በ2022 ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ ለሚያደርጉት የሕክምና ክትትል ትኩረት ለመስጠት ሲሉ በቅድሚያ ጡረታ መውጣታቸው የሚነገርላቸው አቶ ተወልደ፣ አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የኢንዱስትሪ ተደማጭነት እና ተሰሚነት ከፍተኛ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ተጠቁሟል።
የአቶ ተወልደ ወደ ፓኪስታን አየር መንገድ መምራት መነጋገሪያ ከመሆኑ ወራቶች አስቀድሞ ፣ ሌላኛው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ቁንጮና አንጋፋ መሪ አቶ ግርማ ዋቄ በተመሳሳይ መልኩ የኡጋንዳን ብሔራዊ አየር መንገድ ለመታደግ በኃላፊነት ላይ መሾማቸው ይታወሳል።
