- የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኦማን ውስጥ የሚገኝ የአሜሪካ የባሕር ኃይል መከታተያ ራዳር ሥፍራዎችን እንዲሁም ኩዌት እና ባሕሬን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን መምታቱን አስታወቀ።
- ሶርያ ውስጥ የሚገኝ የአሜሪካ የልዩ ዘመቻ ዕዝ ማዕከል ላይም ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።ኦማን ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት “የባሕር ኃይል የቁጥጥር ራዳር እና የአሜሪካ አየር መቆጣጠሪያ ራዳር” መመታታቸውን ዘቡ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
- “በኃይል የሚፈጸሙ የአጸፋ ዘመቻዎች ይቀጥላሉ። የሆርሙዝ ወሽመጥም በአብዮታዊ ዘቡ ባሕር ኃይል ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ቀጥሏል” ብሏል።
- የአሜሪካ የልዩ ዘመቻ ዕዝ ማዕከል ላይ ተፈጽሟል በተባለው የሶርያው ጥቃት፤ “የራዳር ሥርዓት፣ በርካታ የልዩ ሄሊኮፕተሮች እና በርከት ያሉ አሜሪካውያን ኃይሎች” ዒላማ መደረጋቸውን ጠቅሷል።
- እንደ አብዮታዊ ዘቡ ገለጻ፤ በዮርዳኖስ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው አል ታንፍ የተፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት፤ ከሁለት ቀናት በፊት በኢራናውያን ወታደሮች ላይ ለተፈጸመው ግድያ የአጸፋ እርምጃ ነው።
- ሶርያም ሆኑ አሜሪካ እስካሁን ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት አስተያየት አልሰጡም።የዮርዳኖስ ጦር ግን ወደ አገሪቱ የተወነጨፉ ሦስት የኢራን ሚሳዔሎችን ጉዳት ወይም ውድመት ሳይደርስ መትቶ መጣሉን አስታውቋል።
- ኢራን አብዮታዊ ዘብ አዲሱን ጥቃት ከመፈጸሙ አስቀድሞ አሜሪካ “በርካታ የኢራን ጦር ዒላማዎችን” መምታቷን ገልጻለች።
- ኢራን በበኩሏ ድልድዮች፣ ባቡር ጣቢያ እና የአየር ማረፊያን ጨምሮ በተለያዩ የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደተፈጸመባት አስታውቃለች።
- ሁለቱም አገራት የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እየተባባሱ ባሉበት በዚህ ወቅት፤ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን እንደተዘጋ ነው።
ኢራን በኦማን፣ ኩዌት፣ ባሕሬን እና ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን መምቷን አስታወቀች
Date:
