” ሶስት አሠልጣኞችን በአንዴ ማጣት እንደ ሀገርም እንደ አትሌቲክሱም ትልቅ ኪሣራ ነው”

Date:

                             ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በአለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ለመሳተፍ ይዟቸው ከተጓዙት አራት አሠልጣኞች መካከል ሶስቱን ከ16 አትሌቶች መካከል አራቱን ፖርትላንድና ቺካጎ ኤርፖርት ጥሎ ወደ ሀገር ቤት መመለሱ ይታወሳል።

ወደ ሀገር ቤት በተያዘላቸው የጊዜ ሠሌዳና በተቆረጠላቸው ትኬት መሠረት መመለስ ሲገባቸው እዛው አሜሪካን ሀገር የቀሩትና የኮበለሉትን አሠልጣኞችና አትሌቶች ለመመለስ በወቅቱ የቡድን መሪዋ መሠረት ደፋርና የፅ/ቤት ኃላፊው ዶክተር አመንሲሳ ከበደ ለፖሊስ አመልክተው በብስክሌት ጭምር ቢታሠሱም አንዳቸውንም ማግኘት ሳይቻል ቀርቷል።

አራቱ አትሌቶችና ሶስቱ አሠልጣኞች ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ ከቡድኑ ተለይተው ከጠፉ ዛሬ ሰባተኛ ቀናቸውን ቢይዙም ፌዴሬሽኑ በተለይም ፕሬዝዳንቱ ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በስልክ ጭምር አግኝቶ ለማነጋገርና አሳምኖ እንዲመለሱ ጥረት ቢያደርግም አንዳቸውም ስለመመለሳቸው ማረጋገጫ ሲሠጡ አልታየም።

የአትሌቶችና የአሠልጣኞች ኩብለላ ካስደነገጣቸውና ለከፋ ሀዘን ካደረጋቸው አንዱ የሆነው የባለብዙ ታሪክና ውጤት ባለቤት እንዲሁም ከስኬታማ አትሌቶች ጀርባ የሚገኘው ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ ይጠቀሳል።

“በአትሌቶች በተለይ በሶስቱ አሠልጣኞች መኮብለል በእጅጉ አዝኛለሁ፤በቀጣይም ለአሠልጣኞች ተገቢውን ክብር ካልሠጠንና አያያዛችንን ካላሳመርን ኩብለላው ይቀጥላል።

“በማለት በቁጭት የሚናገረው ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ”መጥፋታቸው የሶስት ወር ቪዛቸው ሲጠናቀቅ ቢሆንም እነዚህ የጠፉት አሠልጣኞች በትምህርት ደረጃቸው ሁለተኛ ድግሪ ላይ የደረሡ፣በአሠልጣኝነት ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ፣ብዙ ክለቦች ላይ የለፉና ውጤታማ አትሌቶችን ያፈሩ ሀገር በትልቅ ደረጃ የምትጠብቃቸው አሠልጣኞች ናቸው።

በዚህ ደረጃ በዕውቀትም በስልጠናም የታጠቁ ያውም ሶስት አሠልጣኞችን በአንዴ ማጣት እንደ ሀገርም እንደ አትሌቲክሱም ትልቅ ኪሣራ ነው”ብሏል።

“በሀገራችን ለአሠልጣኞች ተገቢው ክብር አልተሠጠም”በማለት የአሠልጣኞች አያያዝን ደካማና ወደ ስደት የሚገፋ ነው በማለት በአስተያየቱ የሚያማርረው ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ”ይሄ ነገር ስር የሠደደና ለዘመናት አብሮን የኖረ ነው።

ሌላውን ተወውና የሀገር ባለውለተኛውን ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬን ውሠድ ኢትዮጵያን በአለም አደባባይ ከፍ አድርገው፣ያንን ሁሉ አትሌት አፍርተው፣በታሪክ ላይ ታሪክ አፅፈው ህይወታቸው ያለፈው በአልተመቻቸና የሁላችንንም ልብ በሚሠብር መልኩ ነው”

የሚለው ረዳት ኮሚሽነሩ”በተለይ በመጨረሻ ሠዓት ህይወታቸው ሊያልፍ ሲል ገንዘብ ሳይቀር ተዋጥቶላቸው በሚያሳዝን መልኩ ማለፋቸው በቁጭት የምናነሳው የቅርብ ጊዜ ክፉ ትውስታችን ነው”ሲልም ተናግሯል።

“አሁን ያለው የአሠልጣኝ አያያዝና ተገቢውን ክብር ያለመስጠት ችግር በፍጥነት ካልተቀረፈ ውጤት መጠበቅም የዋህነት ነው ስደቱም ከመቀነስ ይልቅ ተጠናክሮ መቀጠሉ አይቀሬ ነው”የሚለው ውጤታማው አሠልጣኝ ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ”መፍትሄ ባይገኝም ከዚህ በፊትም ደጋግሜ ተናግሬያለሁ።

የአትሌቲክስ አሠልጣኝ ከእግር ኳስ አንፃር የሚሠጠውን ክብርና ጥቅም እንኳን ብናየው እጅግ አነስተኛና የሚያሳዝን ነው፤ለአትሌቲክስ አሠልጣኝ የሚሠጠው ትልቁ ደሞዝ 20ሺ ብር ነው፤በአብዛኛው ከ15ሺ ብር የበለጠ አያገኙም በዚህ የኑሮ ውድነት እንዴት ነው ተብቃቅተው ሊኖሩ የሚችሉት ሊገርመን የሚገባው ባይጠፉ ነበር”።

ካለ በኋላ”አሁንም ለአሠልጣኝ ተገቢው ክብርና ከጊዜው ጋር የሚሄድ ተመጣጣኝ ነገር የማይሠጥ ከሆነ ውጤት ማግኘት ይናፍቀናል፣የተሻለ ህይወት ፍለጋ ስደቱም ይቀጥላል፣መቆሚያም አይኖረውም”ብሏል።

“ቀደም ሲል አሠልጣኞቹን የሚያነሳሳ የመሬት፣የመኪናና ዳጎስ ያለ ሽልማት ነበር አሁን የት ነው ያለው?ለአሠልጣኝ የሚሠጠው ክብርስ የት ነው ያለው?”በማለት የሚጠይቀው ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ”እንዴት ይሄን ሁሉ አስቀርተህ በ15 እና 20ሺ ብር ደሞዝ ውጤት እንዲያመጣና በአገኘው አጋጣሚ ከመኮብለል እንዲቀርስ ትጠብቃለህ?”።

“እነዚህ በዕውቀት የተሞሉ አሠልጣኞች የመኮብለል የመጨረሻ ውሳኔን የወሠኑት ሀገራቸውን ስለሚጠሉ አይደለም፣በስራቸው ልክ ተገቢው ክብርና ተመጣጣኝ ነገር ባለማግኘታቸው ነው የሚወዷትን ሀገር ጥለው እስከ መሠደድ የደረሡት።

አሠልጣኞች ላይ ኋላቀር አመለካከት እስካልተከበረና እስካልተቀየረ ድረስ ቢሠደዱ ሊገርመን አይገባም”ሲል ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ ቁጣና ምሬት በተሞላበት አስተያየቱ በመጨረሻ ተናግሯል።

✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል”

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ቱርክ ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ አወጣች

ቱርክ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ዓለም አቀፍ...

በመቀለ የሚካሄደው የአሸንዳ በዓል የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተሰረዘ

በትግራይ በርካታ ታዳሚ በሚገኝበት በየዓመቱ የሚከበረው የአሸንዳ ባህላዊ በዓል...

የኢትዮጵያ ፖስታ 3 ሺሕ የሚጠጉ ቅርንጫፎቹን ወደ ባንክ ኤጀንትነት ለመቀየር እንቅስቃሴ ጀመረ

የኢትዮጵያ ፖስታ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ 3 ሺሕ በሚጠጉ ቅርንጫፎቹ...

«ግብጽ ዛቻውን አቁማ ወደ ድርድር ትግባ!»

ታዋቂው የአፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ዴቪድ ማትሳንጋ ግብጽ በኢትዮጵያ...