ወደ አሜሪካ የተጓዘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ልዑክ፣ በሁለቱ አገራት መካከል “የመከላከያ እና ደኅንነት ዘርፍ አጠቃላይ ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዲመሠረት” የሚያስችል ስምምነት መፈጸሙ ተገለጸ።
ከአሜሪካ ጋር የተደረሰው የሁለትዮሽ የመከላከያ ስምምነት “ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ” እንዲሁም “በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ” ላይ የተመሠረተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አርብ ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው፤ በመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ የተመራ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎችን ልዑክ ወደ አሜሪካ ተጉዟል።
ልዑኩ ረቡዕ እና ሐሙስ በነበረው የአሜሪካ ቆይታ፣ ከአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት አመራሮች ጋር “የሁለትዮሽ የጋራ ምክክሮችን” ማድረጉ ተገልጿል። ምክክሩ የተመራው በአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት ሚኒስትር ብራያን ጄ. ኤሊስ እንደሆነም መግለጫው ጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ወደ አዲስ እና የላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ስምምነት ላይ ተደርሷል” ብሏል። ሁለቱ አገራት የመከላከያ “ተቋማዊ ትብብርን ለማስፋፋት እና ስትራቴጂካዊ ቅንጅትን የበለጠ ለማጠናከር” ተስማምተዋል።
የአሜሪካ እና ኢትዮጵያ “አጠቃላይ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር” ከሚመራባቸው አምዶች አንዱ፤ “ብሔራዊ ጥቅሞችን እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ” የሚለው ነው። “የጋራ መተማመንን በማጠናከር ዘላቂ ትብብር መመሥረት” ሌላኛው የትብብሩ መሠረት እንደሆነ ተገልጿል።
ሁለቱ አገራት ትብብራቸው “በአፍሪካ ቀንድ እና በሰፊው ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ የጋራ ጥረቶችን ማጠናከርን” መርሆ እንዲያደርግ ተስማምተዋል ተብሏል።
ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ እና ምክትል ረዳት ሚኒስትር ብራያን ጄ. ኤሊስ ስምምነት የተደረሰባቸው “ማዕቀፎችን በፍጥነት ለመተግበር” ቁርጠኝነታቸውን ማረጋገጣቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። “ሁለቱዮሽ የመከላከያ ግንኙነቱን ወደ የተሻለ እና ወደፊት ላይ ያተኮረ ስትራቴጂካዊ አጋርነት” እንዲሆንም መስማማታቸው ተገልጿል።
አዲስ አበባ እና ዋሽንግተን ባለፈው ግንቦት ላይ የተፈራረሙት የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነትም በተመሳሳይ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች አንዱ “የመከላከያ እና ፀጥታ ትብብር” ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ወደ አሜሪካ ተጉዘው የፈጸሙት ይህ ስምምነት፤ “በፀጥታ ጉዳይ ትብብርን ለማጠናከር እና በጋራ የደኀንነት ጉዳዮች ዙሪያ ተሳትፎን ለማጠናከር” ምክክሮች እንዲደረጉ የሚያስችል ነበር።
