ትናንት ( ቅዳሜ ጥቅምት 14 2019 ዓ.ም ) የቀድሞ ኤዲተሬ ከአሜሪካ መጥቶ ምሳ ሊጋብዘን አራት ኪሎ ተቀጣጠርንነበር። ከ ዳንኤል ድርሻ ጋር በABBIY Weekly, በዕንቁ መጽሔት በጋራ ሠርተናል። ኤዲተሬና ብዙ የነፃውን ፕሬስ ታሪክ ያሳለፈ፣ የመከራውን ዘመን ያሳለፍን ሰዎች ነን። የሠሎሞን ለማ የዳንኤልም የኔም የሌሎችም ሰብሳቢ የነበረው ደግሞ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ነበር።
ፍቄ (ባሪያው) በነፃው ፕሬስ ታሪክ ጉልህ አሻራ የነበረው ሰው ነበር። የአብዛኞቹ ጋዜጣና መጽሔት አከፋፋይ፣ የገበያውም መሃንዲስ፣ ከጊዜ በኋላም የራሱ መጽሔቶች ባለቤት ነበር። በችግራችን ወቅት ደራሻችንም ፍቄ ነበር።
ከ1997 በኋላ በነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች መከራ ሲወድቅ ደጋፊያችንም ነበር። በተለይ ዕንቁ እና ግዮን መጽሔቶችን እያዘጋጀ ከቢሮክራሲው ጋር እየታገለ፣ እየታሠረ እየተፈታ ሥራውን ለማስቀጠል ብዙ ታግሏል። ልክፍት ሆኖበትንጂ በጋዜጣና መጽሔት ሽያጭ ሃብት እንደማይገኝ በረጅም ጊዜ የሥራ ልምዱ ያውቀዋል። ኪሣራ እንጂ ትርፍ የሌለው ቢዝነስ ቢኖር ነጋዜጣና የመጽሔት ሽያጭ ነው።
ሪፖርተር” ስ ትሉኝ ይሆናል። ዘልቄ ባላውቅም አማረ አረጋዊ ወሬ ሽጦ ጋዜጣውን ሊያቆየው አይችልም። ጨረታው፣ ማስታወቂያው ወይም ሌላ ቢሆን እንጂ። ወሬ ተሽጦ ኑሮ አይገፋም። ያውም በርካታ ሠራተኞችን እያስተዳደረ።
ፍቄ ዛሬም ድረስ ከዚህ የመጽሔት ዝግጅት አልተላቀቀም። ቢሮ ተከራይቶ ሠራተኞች ቀጥሮ ሥራ እየሠራ ነው። ዛሬ ከሪፖርተር ውጪ ጋዜጣ እያየሁ አይደለም። ከግዮን ውጪ መጽሔት አላየሁም። (ምናልባት ቢኖር ከእኔ አለማየት አኳያ ይታይልኝ)
ፍቄ ማን ሊገዛ ነው የሚያሳትመው?፣ ምን ያህል አንባቢ ኖሮ ነው የሚያሳትመው? በዚህ ውድ ዘመን በስንት አሳትሞ ስንት ሊሸጠው ነው? እያልኩ ስብሰለሰል ለዚህ ሥራ ሲል ሁለቱንም መኪኖቹን መሸጡን ስሰማ ቀልቤ ስብር አለ።
ሌላው ዓለም ዲጂታል ሚዲያ ቢስፋፋም ፕሪንቲንግ ሚዲያ አልቆመም። አውሮፓ አሜሪካን ትተን እዚህ ጎረቤት አገር ኬንያ “ዴይሊ ኔሽን” ጋዜጣ ዛሬም እየታተመ ይሸጣል። እኛ አገር ከፕሬስ አፈናው ባሻገር ዘመን የወለደው ማኅበራዊ ሚዲያ ሰውን ከጋዜጣና መጽሔት ገፍትሮ አስወጥቶታል። ታዲያ ፍቄ ንብረቱን ሁሉ እስኪያስጨርሰው ለምን ገፋበት?
መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው። ማኅበረሰቡ አማራጭ ሚዲያን ሊያጣ አይገባውም የሚል የልጅነት ልክፍት። በዚህ ሥራ ብዙ መሥዋእትነት ከፍሎበታል ጭራሽ ንብረት እስከማሸጥ ካደረሰው እኛን እየወቀሰን ነው። በመጻፍ፣ በማንበብ፣ በመግዛት፣ ማስታወቂያ እየሰጠን መደገፍ ባለመቻል፣ ሥራውን በመደገፍ ከጎንህ አለን ማለት ባለመቻላችን እየወቀሰን ያለ መሠለኝ። ሁሌም የሚሠራን ሰው ለወቀሳ እንፈጥናለን። ታጋይን ለመደገፍ ግን ሸርተት ባዮች ነን። እኛ ቸልተኞች፣ እኛ ጠንካራን ገፍታሪዎች፣ ከወደቀ በኋላ ከንፈር መጣጮች፣ ካለፈ በኋላ የሕሊና ባለእዳዎች ዞር ብለን አለማየታችን ነው ፍቄን ንብረቱን ያሸጠው። የሸጠውን መመለስ አለበት።
ትናንት በሰዓት ፍቄ ባይኖርም ቢሮውን ጎበኘን፣ ትጋቱን አየን፣ ጥንካሬውን አደነቅን ራሳችንን ወቅሰን ወዳጆቼን ትቼ ወደ አጣዳፊ ሥራዬ በረርሁ። በመላው ዓለም የምንገኝ የሚዲያ ሰዎች ባለሃብቶች፣ አንባቢያን ፍቃዱን ምን እየሠራህ ነው በምን እናግዝህ እንበለው።
